በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ምክትል ፕሬዚደንት ካማላ ሐሪስ በስዊዘርላንድ በሚካሂደው የዩክሬይን ጉባዔ ይካፈላሉ


ፎቶ ፋይል፡ የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚደንት ካማላ ሐሪስ ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ጋር በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡ ወቅት በሙኒክ፣ ጀርመን፣ እአአ የካቲት 17/2024
ፎቶ ፋይል፡ የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚደንት ካማላ ሐሪስ ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ጋር በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡ ወቅት በሙኒክ፣ ጀርመን፣ እአአ የካቲት 17/2024

የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚደንት ካማላ ሐሪስ እና የ ኋይት ሐውስ የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪው ጄክ ሰለቫን እአአ ሰኔ 15 ቀን ስዊዘርላንድ ውስጥ በሚካሄደው የዩክሬይን ጉባዔ ላይ እንደሚገኙ ኋይት ሐውስ ትናንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ምክትል ፕሬዚደንት ሐሪስ ወደስዊዘርላንድ የሚጓዙት ዩክሬይን ሉዓላዊነቷን እና የግዛት አንድነቷ እንዲሁም የተ መ ድ ቻርተር መሠረት ባደረገ መንገድ ፍትሀዊ እና ዘላቂ ሰላም ለማግኘት የያዘችውን ጥረት ዋሽንግተን እንደምትደግፍ በድጋሚ ለማረጋገጥ መሆኑን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተራቸው ክሪስቲን አለን አመልክተዋል። የዩክሬይን ህዝብ ሩሲያ የቀጠለችውን ወረራ ለመመከት የሚያደርገውን ትግል ዩናይትድ ስቴትስ ትደግፋለች ብሏል።

ክሬምሊን ስለዩክሬይን ሰላም የሚደረግ ንግግር ሩሲያን ማሳተፍ እንዳለበት በተደጋጋሚ ይናገራል። ሩስያ በስዊዘርላንዱ ጉባዔ እንድትሳተፍ አልተጋበዘችም።

ቻይናም ሩሲያን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች እኩል የሚሳተፉበት ጉባዔ እንዲካሄድ ጥሪ ስታቀርብ ቆይታለች። ሩሲያ ሩሲያ ከዩክሬይን ግዛቶች እንድትወጣ የሚጠይቀውን የዩክሬይን ፕሬዚደንት ዜሌንስኪን የሰላም ዕቅድ " የማይሳካ" ብላዋለች።

ፊሊፒንስ በጉባዔው ላይ እንደምትሳተፍ ትላንት ሰኞ ያስታወቀች ሲሆን የዩክሬይን ፕሬዚደንት ዜለንስኪ ስለምትሰጠው ድጋፍ አመስግነዋል።

ዜለንስኪ ዕሁድ ዕለት ሲንጋፖር ውስጥ በተካሄደ የጸጥታ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር ቻይና በስዊዘርላንዱ የሰላም ጉባዔ ላይ ሌሎች ሀገሮች እንዳይገኙ ተጽዕኖ በማድረግ ሩሲያ ጉባዔውን ለማክሸፍ የያዘችውን ሙከራ በመርዳት ላይ ናት ሲሉ ተናግረዋል።

ቻይና በዩክሬይን ጦርነት ጉዳይ ገለልተኛ እንደሆነች ትናገር እንጂ ከሩሲያ ጋር የንግድ ግንኙነቷ እያደገ በመሆኑ ሞስኮ የምዕራባዊያን ማዕቀቦች እንድትቋቋም ዕድል ሰጥቷታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጣሊያን ሁለተኛ ዙር የአየር ጥቃት መከላከያ አቅርቦት ለዩክሬይን ሳትልክ እንደማትቀር ተነግሯል።

በተያያዘ ዜና ዩክሬይን ዩናይትድ ስቴትስ አንዳንዶቹ የጦር መሣሪያዎቿን አስመልክታ ያስቀመጠችውን ገደብ በከፊል ማንሳቷን ተከትሎ ሌሎችም አጋሮቿ ወታደሮቿ ሩሲያ ግዛት ያሉ ኢላማዎችን እንዲያጠቁ ተጨማሪ ነጻነት እንዲሰጡላት ጥሪ አቅርባለች።

በሌላ በኩል የስዊዘርላንድ ፓርላማ ለዩክሬይን ሊሰጥ የታቀደውን የ5 ነጥብ 58 ቢሊዮን ዶላር የዕርዳታ መዋጮ የብድር ገደባችንን ይጥሳል በማለት ከልክሏል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG