በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሦስት የአውሮፓ ሀገሮች መሪዎች ወደዩክሬን መዲና ኪየቭ እየተጓዙ ናቸው


ኪየቭ ዩክሬን ውስጥ የቦምብ ጥቃት በተፈፀመበት ህንፃ ላይ የእሳት አደጋ ሰራተኞች እሳቱን እያጠፉ እአአ መጋቢት 15/2022
ኪየቭ ዩክሬን ውስጥ የቦምብ ጥቃት በተፈፀመበት ህንፃ ላይ የእሳት አደጋ ሰራተኞች እሳቱን እያጠፉ እአአ መጋቢት 15/2022

ሩሲያ መውረሯን ከሦስት ሳምንት ገደማ በፊት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ኃይሎቿ ኪየቭን እና ሌሎችንም ከተሞች መደብደባቸውን ቀጥለዋል። ዛሬ ማለዳ የሩሲያ ኋይሎች ኪየቭ ላይ ባደረሱት የመድፍ ጥቃት አንድ የመኖሪያ ህንፃ መትተው ቢያንስ ሁለት ሰዎች ገድለዋል። የመዲናዋ ከንቲባ ቪታሊ ክሊትሽኮ ከዛሬ ማታ ጀምሮ ለሰላሳ ስድስት ሰዓት የሚዘልቅ የሰዓት እላፊ አውጀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የቼክ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ፒትር ፊያላ ከፖላንድ አቻቸው ማቱዌዝ ሞራውችኪ እና ከስሎቬንያው አቻቸው ያኔዝ ያንሳ ጋር ሆነው ወደሊቭ እንደሚጓዙ ዛሬ አስታውቀዋል። የሚሄዱትም የአውሮፓ ካውንስልን ወክለው ከዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ዴኒስ ሽሚሃል ጋር ለመወያየት መሆኑን አስታውቀዋል።

"የጉብኝታችን ዓላማ መላው የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን ሉዓላዊነት እና ነፃነት ያለውን የማያወላውል ድጋፍ ለማረጋገጥ ነው፣ ለዩክሬይን እና ለህዝቧ ስፋት ያለው ድጋፍ ለማቅረብም ነው" ብለዋል የቼክ ሪፐብሊኩ ጠቅላይ ሚኒስትር። የፖላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር በበኩላቸው "በዚህ በዓለማችን ታሪክ ወሳኝ የሆነ ወቅት ቦታው ላይ መገኘታችን የግድ ነው፣ ለኛ ብለን የምናደርገው አይደለም ልጆቻችን ከጭቆና ነጻ በሆነች ዓለም ሊኖሩ ስለሚገባ ነው" ብለዋል።

የአውሮፓ ህብረት ሩሲያ ላይ አዲስ ዙር ማዕቀብ አውጇል። ማዕቀቡ ከአንዳንዶቹ የሩሲያ መንግሥታዊ ኩባኒያዎች ጋር መናገድን እና በዚያች ሀገር የኤነርጂ ዘርፍ አዲስ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስን ይከለክላል፣ በሩሲያ የብረት እና የቅንጦት ዕቃዎች ላይም የንግድ ገደቦቹን አጥብቋል።

በዋና ዋናዎቹ የፖለቲካ ተደማጭነት ያላቸው ቱጃሮች ሎቢይስቶችና የክሬምሊንን ፕሮፓጋንዳ በሚያናፍሱ ግለሰቦች እና የአቪየሽን እና የመርከብ ግንባታ ኩባኒያዎች ላይ ያነጣጠሩ ማዕቀቦችም ተጥለዋል።

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል "አራተኛው ማዕቀብ ሩሲያ የዩክሬን ወረራዋን ለማካሄድ የምትተማመንበት የኢኮኖሚ እና የሎጂስቲክስ መሰረቷን በከባዱ ለመምታት የታለመ መሆኑ እና ፑቲን ይህን ኢሰብዓዊ ጦርነት እንዲያቆሙ ግፊት ለማድረግ ነው" ብለዋል።

ለወረራው የተሰጡት ዓለም አቀፍ ምላሾች ሩሲያን በኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦች መቅጣት ላይ ያተኮሩ ሲሆን ጃፓን አስራ አንድ የፓርላማ አባላት ያሉባቸው አስራ ሰባት ሩስያውያን ንብረት እንዳይንቀሳቅሰ ማገዷን ዛሬ አሳውቃለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩሲያ እና የዩክሬን ተደራዳሪዎች ትናንት ቤላሩስ ላይ የጀመሩትን ንግግር ዛሬ እንደትናንቱ በአካል ሳይሆን በቪዲዮ አማካይነት ይቀጥላሉ። የዋይት ኃውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል ዩናይትድ ስቴትስ ድርድሮቹን ትደግፋለች ብለው ይሁን እና ከድርድሮቹ ጎን ጥቃቱን በረድ ለማድረግ ፈቃደኛ ትሆን እንደሆን እየተከታተልን ነን ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከኔቶ መሪዎች ጋር ስለጦርነቱ ለመወያየት ወደብረሰልስ ይጓዛሉ የሚሉ ሪፖርቶችን ጄን ሳኪ ለማረጋገጥ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ፕሬዚዳንቱ ለዩክሬን አጣዳፊ ወታደራዊ እና ሰብዓዊ እርዳታ የተመደበ 13 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ያካተተ ወጪ ዛሬ ይፈርማሉ ተብሏል። ነገ ደግሞ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ለዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስ ንግግር ያደርጋሉ። ፕሬዚዳንቱ የዩክሬን የአየር ክልል ለበረራ ክልክል ቀጣና እንዲታወጅ መጠየቃቸው እና የባይደን አስተዳደር እንዳልተቀበለው ይታወቃል።

XS
SM
MD
LG