በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“የኔቶ አባላት የረጅም ርቀት ሚሳኤል ስለመጠቀም መናገራቸው አደገኛ ነው” ክሬምሊን


ፎቶ ፋይል፦ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ
ፎቶ ፋይል፦ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ

በያዝነው ሳምንት ዋሽንግተን ዲሲ ጉባኤ ተቀምጠው የነበሩት የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዓባላት የረጅም ርቀት ሚሳዬል ስለ መጠቀም ማውሳታቸው “አደገኛ ማባባስ” ነው ሲሉ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ዛሬ ዓርብ ተናግረዋል።

ከኔቶ ዋና ፀሐፊ ጀንስ ስቶልተንበርግ ጋራ ሆነው ትላንት ሐሙስ መግለጫ የሰጡት የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜሌኒንስኪ፣ ሃገራቸው ሩሲያ ውስጥ ድረስ የዘለቀ ጥቃት ማድረግ ትችል ዘንድ፣ የርጅም ርቀት መሣሪያዎችን በመጠቀም ላይ አሜሪካ የጣለችውን እገዳ እንድታነሳ ጠይቀዋል።

ዩክሬን በአሁኑ ወቅት ከአሜሪካ ባገኝችው መሣሪያ ማድረግ የምትችለው፣ በሩሲያ ድንበርና አካባቢ የጥቃት መነሻ በሆኑት ቦታዎች ላይ የመልስ ጥቃት መፈፀም ነው።

ዜሌንስኪ ትላንት በተደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሉት፣ ሃገራቸው በአሸናፊነት ለመወጣትና ራሷን መከላከል ትችል ዘነድ በረጅም ርቀት መሣሪያዎች ላይ በአሜሪካ የተጣለው እገዳ መነሳት አለበት፡፡

ከዜና ሰዎች ጋራ ክሬምሊን ውስጥ በስልክ የተነጋገሩት ዲሜትሪ ፔስኮቭ፣ ሃገራቸው የኔቶን ጉባኤ በጥንቃቄ እንደተከታተለችና፣ የረጅም ርቀት መሣሪያዎችን መጠቀም በተመለከተ የተነገረውም “አደገኛ ጠብ ጫሪነት” ነው ብለዋል።

ቀድሞ በዩክሬን ውስጥ የነበሩ፣ አሁን ግን ሩሲያ እንደግዛቷ በምትቆጥራቸው በሉሃንስክ፣ ዶነስክ፣ ኬርሶን እና ዛፖሪዤዥያ የረጅም ርቀት ሚሳዬሎች ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሆነ ያወሱት ፔስኮቭ፣ ከዚህ የበለጠ ርቀትን ለመምታት ማሰብ “ፍፁም ትንኮሳ” ነው ብለዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG