በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሩስያ ኦዴሳ ወደብ ላይ የድሮን ጥቃት ማድረሷን ዩክሬን ተናገረች


ፎቶ ፋይል፦ የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ፉሚዮ ኪሺዳ
ፎቶ ፋይል፦ የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ፉሚዮ ኪሺዳ

ጃፓን ከሩስያ ጋር ጦርነት ላይ ላለችው ለዩክሬን የ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ልትሰጥ ቃል ገባች፡፡ እርዳታውን ትናንት ሐሙስ ይፋ ያደረጉት የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ፉሚዮ ኪሺዳ ከዚያ ውስጥ 1 ቢሊዮን ዶላሩ ለሰብዐዊ እርዳታ የተመደበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ሩስያ በዩክሬን ኦዴሳ ክፍለ ግዛት ላይ ባደረሰችው የድሮን ጥቃት አንድ ሰው ስትገድል የወደቡ ህንጻ ላይ ጉዳት ማድረሷን የኦዴሳ አስተዳዳሪ ትናንት ሐሙስ ገልጸዋል፡፡ የዩክሬን የአየር ጥቃት መከላከያ ኅይል አብዛኞቹን በራሪ አልባ አውሮፕላኖች መትቶ ሲጥል የተወሰኑት አምልጠው ጥቃቱን ማድረሳቸውን አገረ ገዢው አመልክተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናይትድ ስቴትስ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ሪፐብሊካን አባላት ለዩክሬን እና ለእስራኤል እንዲሁም ለዩናይትድ ስቴትስ ደቡባዊ ድንበር ጥበቃ የቀረበውን የ 110 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ዕቅድ ከልክለዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ዩክሬን እና እስራኤል ውስጥ ለሚካሄዱት ጦርነቶች እንዲሁም ለዩናይትድ ስቴትስ የድንበር ደህንነት ጥበቃ የሚውል ወደ 106 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ ምክር ቤቱ እንዲፈቅድ ጠይቀዋል፡፡

ከትናንት በስተያ ረቡዕ ድምጽ የሰጡት የህግ መወሰኛው ምክር ቤት አባላት 49ኙ እርዳታውን ሲደግፉ 51ዱ ተቃውመዋል፡፡ በመሆኑም የእርዳታው ዕቅድ ለማለፍ የሚያስፈልገውን 60 የድጋፍ ድምጽ አላገኘም፡፡

ለዩክሬን እርዳታ እንዲሰጥ የሚደግፉት የመወሰኛ ምክር ቤቱ የሪፐብሊካኖች መሪ ሚች መኮኔል ሆኖም የእርዳታው ጥቅል ለዓመታት የታገልንላቸውን ፖሊሲዎች የሚቀይሩ እርምጃዎች ያካተተ በመሆኑ እንዳትደግፉ ብለው የፓርቲያቸውን አባላት ማሳሰባቸው አይዘነጋም፡፡

ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ረቡዕ ቀደም ብለው በሰጡት ቃል “ምክር ቤቱ ለዩክሬን የታቀደውን እርዳታ ሳይደግፍ ቢቀር ጎረቤት ሀገር ላይ ጦርነት ለከፈቱት ለሩስያው ፕሬዚደንት ቪላዲሚር ፑቲን ዩናይትድ ስቴትስ ትልቅ ስጦታ እንደሰጠቻቸው ይቆጠራል” ብለው ነበር፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG