የሩሲያ የሰው አልባ አውሮፕላን(ድሮን) ሌሊቱን ባካሔደው ጥቃት፣ በአገሪቱ ማዕከላዊ ክፍል ፖልታቫ ግዛት የሚገኘውን የነዳጅ ዘይት ማጣሪያ እንዳጠቃ፣ ዩክሬን፣ ዛሬ ረቡዕ አስታወቀች፡፡
የግዛቲቱ አገረ ገዥ ዲምትሮ ሉኒን፣ በተቋሙ የሚከናወነው ሥራ ለጊዜው እንደተቋረጠ ተናግረዋል፡፡
በጥቃቱ ስለደረሰው ጉዳት አልተገለጸም፡፡
የድኒፕሮ ፔትሮቭስክ ግዛት ገዥ ሼሪ ሊያስክ፣ ሩሲያ፣ ኒኮፖልንና ሦስት አካባቢዎችን በማጥቃት በአምስት ቤቶች ላይ ጉዳት ማድረሷን ተናግረዋል፡፡
የዩክሬን ጦር የአየር ኀይል፣ በምሽቱ ጥቃት ከተሳተፉ 24 የሩሲያ ሰዋልባዎች(ድሮኖች) ውስጥ 17ቱን መቶ እንደጣለ አስታውቀዋል፡፡
ዩክሬን፣ የሩሲያን የመከላከያ መስመር ለመስበር ስታደርግ የቆየችው ጥረት፣ በቅርቡ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቁ በነበሩት የጦር መሣሪያዎች ምላሽ እንደሚያገኝ ተመልክቷል፡፡
አንዳንዶቹ፣ ባለፈው ጥር ወር ቃል የተገቡት ዩናይትድ ስቴትስ ሥሪት 31-ኤምዋን(M1) አብርሃም ታንኮች ናቸው፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስተን፣ አገራቸው የምትመራውና 50 አገሮች የተሳተፉበት የዩክሬን መከላከያ ግንኙነት ቡድን ስብሰባ፣ ትላንት ማክሰኞ በጀርመን ሲካሔድ፣ ዩክሬን በአሁኑ ጊዜ የሚያስፈልጋትን ሁሉ ማግኘቷን እንድትቀጥል፣ “የማይደረግ ነገር አይኖርም፤” ብለዋል፡፡
መድረክ / ፎረም