በሩሲያውያን የሚታዘዙ ኢራን ስሪት ድሮኖች ዛሬ ሀሙስ የሃገሪቱን ዋና ከተማ አካባቢዎች መደብደባቸውን የዩክሬን ባለሥልጣናት ተናገሩ፡፡
የዩክሬን ወታደራዊ ክፍልም የሩሲያ ሚሳዬሎች ዩክሬናውያን በሚኖሩባቸው 40 የተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ቀደም ብሎ በነበረው ቀን ድብደባ መፈጸማቸውን አስታውቋል፡፡
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ ካይሮሎ ታይመሰንኮ ድሮኖቹ በኪየቭ ዙሪያ የሚገኙ “ወሳኝ የመሰረተ ልማት ተቋማትን” መደብደባቸውን ተናግረዋል፡፡
ባለሥልጣናቱ “ካሚካዜ” ብለው የሚጠሯቸው ሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖቹን (ድርኖች) ራሳቸውን ከዒላማዎቻቸው ጋር የሚያላትሙ ፈንጅዎችን የጫኑ አድርገው ገልጸዋቸዋል፡፡
የሚኮላይቭ ከንቲባ አሌክሳንድር ሴንኮቪች በደቡባዊቷ የዩክሬን ከተማ ትናንት ሌሊቱን በተካሄደ ድብደባ ባለ አምስት ፎቅ የአፓርትመንት ህንፃ መወደሙንም አስታውቋል፡፡
የአየር ጥቃቶቹ የተፈጸሙት የዩክሬን አጋሮች ተጨማሪ የአየር መከላከያ መሳሪያዎችን ለዩክሬን ለመስጠት እየሠሩ ባሉበት ወቅት መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌነስኪ “የሩሲያ ሽብር የበለጠ ድፍረትና ጭካኔ የተሞላበት እየሆነ በሄደ ቁጥር፣ ዩክሬን አየር ክልሏን እንድትከላከል መርዳት ለአውሮፓ በዘመናችን ካሉ የላቁ የሰብአዊ ተግባሮች መካከል አንዱ መሆኑን ለዓለም ግልጽ እየሆነ ይመጣል” ሲሉ ትናንት ረቡዕ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡
ብሪታኒያ የክሩዝ ሚሳዬሎችን መትተው መጣል የሚችሉ ሮኬቶችን እንደምትልክ ዛሬ ሀሙስ ስትገልጽ፣ የኔቶ መከላከያ ሚኒስትሮችም ለዩክሬን ስለሚሰጡት ወታደራዊ እርዳታ ለመምከር ብራስልስ ላይ መሰብሰባቸው ተመልክቷል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስትን ትናንት ረቡዕ በሰጡት መግለጫ፣ "የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለ300ሺው ተጠባባቂ ጦር የክተት መርኃግብር “ምንም ሥልጠናና እውቀት የሌላቸውን የሩሲያ ሲቪሎችን አስገድደው ወደ ግንባር ለመላክ ሲሞክሩ፣ ዩክሬን ለዴሞክራሲያቸውና ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር የሚታገሉ ወታደሮችዋንና የነፃ ህዝብ ወታደሮችዋን ኃይል አሳይታለች” ብለዋል፡፡
“ልበ ሙሉነታቸው ሁላችንንም ያነሳሳናል” ያሉት ኦስትን “ፑቲን ጦርነትን መረጡ፡፡ ዩክሬን ግን ራሷን መከላከል መረጠች፡፡ እናም እጅግ በሚያስደንቅ ሁኔታ አደረገችው” ብለዋል፡፡