በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ትረምፕ የሩሲያን ማዕቀብ ፈረሙ


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ሩሲያ ላይ የጣላቸውን አዳዲስ ማዕቀቦች የያዘ ሠነድ ዛሬ ፈርመው የሃገሪቱ ሕግ አድርገውታል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ሩሲያ ላይ የጣላቸውን አዳዲስ ማዕቀቦች የያዘ ሠነድ ዛሬ ፈርመው የሃገሪቱ ሕግ አድርገውታል።

ይሁን እንጂ በሴኔቱ ውሣኔ ላይ ያላቸውን ቅሬታ በግልፅ ያሳወቁት ፕሬዚዳንት ትረምፕ “እጅግ የተዛባ” ና “በግልፅ ኢሕገመንግሥታዊ” ሲሉ ጠርተውታል ውሣኔውን።

ማዕቀቦቹ የተጣሉት ሩሲያ ባለፈው ምርጫ ውስጥ ትረምፕ እንዲመረጡ ለመርዳት ጣልቃ ገብታለች ሲል የተወካዮች ምክር ቤቱ ለደረሰበት ድምዳሜ እንደቅጣት ሲሆን ሁለቱም የምክር ቤቱ ክንፎች ያሳለፉት ይህ ሕግ የውጭ ጉዳዮችን እርሣቸው ምቹ ነው ብለው በሚያስቡት መንገድ ማከናወን እንዳይችሉ እገዳዎችን የጣለ መሆኑንም አመልክተዋል።

ፕሬዚዳንቱ ማዕቀቦቹን ማላላት እንዳይችሉ ኮንግረሱ ዕገዳ በጣለበት ጉዳዩን ለማጥናት በቆረጠው የሰላሣ ቀን ገደብ ባይስማሙም እንደሚያከብሩት ሚስተር ትረምፕ ሰነዱን በፈረሙበት ወቅት አስታውቀዋል።

አዲሱ የማዕቀብ ሕግ ከሩሲያ የጋዝና የነዳጅ ኩባንያዎች ጋር በሚሠሩ የአሜሪካ የንግድ ድርጅቶች ላይ ገደቦችን የሚጥል፣ እንዲሁም የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የወሰዷቸውን የሩሲያን ዲፕሎማቶችን ማባረርና የኤምባሲውን ሁለት ተቋማት መንጠቅን ያካተቱ እርምጃዎች ያፀና ነው።

ለአሁኑና ለቀደሙትም የአሜሪካ እርምጃዎች ምላሽ የሰጠችው ሩሲያ ዋሺንግተን ሩሲያ ውስጥ የሚገኙ ዲፕሎማቶቿንና የኤምባሲና ተልዕኮዎቿ ሠራተኞችን በከፍተኛ ቁጥር እንድትቀንስ አዝዘለች።

ዩናይትድ ስቴትስ ሩሲያ ውስጥ የሚገኙ ዲፕሎማቶቿን ቁጥር በሰባት መቶ ሰው እንድትቀንስ ከክሬምሊን የወጣውን ትዕዛዝ የዩናይትድ ስቴትስ የሕግ ወመሰኛ ምክር ቤት አባላት አናንቀውታል።

ትዕዛዙ ከሞስኮ የወጣው ሩሲያን ባለፈው የሃገራቸው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወቅት ጣልቃ በመግባት የሚከስሱት የአሜሪካ እንደራሴዎች በቅጣት መልክ ላሳለፉት ጥብቅ ማዕቀብ እንደ አፀፋ መሆኑ ተነግሯል።

የሴኔት ሪፖርተራችን ማይክል ባውማን ዘገባ እንደሚጠቁመው ባለፈው ሐሙስ በሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ የታየው የሁለቱም ፓርቲዎች እንደራሴዎች አንድነት እንዲህ በየጉዳዩና በየወቅቱ የሚስተዋልና የተለመደ አይደለም። ዘጠና ስምንት ለሁለት በሆነ ሙሉ ሊባል በሚችል ድምፅ ነው ሴኔቱ የማዕቀቦቹን ውሣኔ ያሳለፈው።

ክሬምሊን የአሜሪካዊያኑ ዲፕሎማቶችና ሠራተኞች ቁጥር በሰባት መቶ እንዲቀንስ ካዘዘ በኋላም ቢሆን የአሜሪካዊያኑ ሕግ አውጭዎች የከረረ አቋም እንዳልተለሳለሰና የእንደራሴዎቹም አንድነት እንዳልተነቃነቀ ሪፐብሊካኗ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሱዛን ኮሊንስ አመልክተዋል።

“መጀመሪያውኑ ዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀቦቹን እንድትጥል ምክንያት የሆኑት የእራሳቸው አድራጎቶች መሆናቸውን ችላ ብለው ፕሬዚዳንት ፑቲን አንዳች የአፀፋ እርምጃ እንደሚወስዱ እጠብቅ ነበር። ሩሲያዊያኑ ጠባያቸውን ሊቀይሩ ይገባል” ብለዋል ሴናተር ኮሊንስ።

ሴኔቱ የጣላቸው ማዕቀቦች በሰሜን ኮሪያና በኢራንም ላይ ያነጣጠሩ ሲሆኑ ማንኛቸውም ዓይነት የቅጣት እርምጃዎችን ለማቅለል የሚደረሱ ውሣኔዎች በቅድሚያ በተወካዮች ምክር ቤቱ መፅደቅ እንደሚኖርባቸው የዴሞክራቶቹ ሕዳጣን ሴናተሮች መሪ ቸክ ሹመር በአፅንዖት ተናግረዋል።

“ያለ ኮንግረሱ ውሣኔ ፕሬዚዳንት ፑቲን ከእነዚህ ማዕቀቦች ማነቆ ሕመም ሊያመልጡ አይችሉም። ለፕሬዚዳንት ፑቲንም ሆነ ለሌላ በእኛ ምርጫ ውስጥ ጣልቃ ለመግባት ለሚያስብ ማንም መንግሥት ይህ ግልፅ መልዕክት ይሁን። እኛ የተቀደሰ አድርገን በምናያቸው ምርጫዎቻችን ውስጥ ጣልቃ ከገባችሁ ማዕቀብ ይጣልባችኋል። እነዚያ ማዕቀቦች ደግሞ የከበዱ ነው የሚሆኑት...” የሴናተር ሹመር ብርቱ መልዕክት ነው።

ኮንግረሱ በወሰዳቸው እርምጃዎች ላይ ጨርሶ ቅሬታ እንደሌላቸው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ሪፐብሊካን አብዝኀ ረዳት መሪ ጃን ኮርኒን ተናግረዋል።

እንዲህ አሉ ኮርኒን፤ “ማዕቀቦቹን በማሳለፋችን ተደስቻለሁ። ፑቲን የሚጫወቷቸው ጥቂት ካርዶች እንዳሏቸው እረዳለሁ፤ ይሁን እንጂ ሁኔታው አብረን ልንሠራባቸው የምንችል አይሲስን መውጋት እና የሽብር ፈጠራ ሥጋትን የመሳሰሉ አካባቢዎች መኖራቸውን ወደመገንዘብ ይወስደናል የሚል ተስፋ አለኝ።”

በክሬምሊን ትዕዛዝ መሠረት ከሥራ ውጭ ከሚሆኑት መካከል ብዙዎቹ እዚያው የተቀጠሩ ሩሲያዊያን ሠራተኞች ሳይሆኑ እንደማይቀሩ ተገምቷል።

በሌላ በኩል ደግሞ በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥ በሚሰጥ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ትናንት ድንገት በአካል የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሬክስ ቲለርሰን መሥሪያ ቤታቸው በሰሜን ኮሪያ፣ በቬኔዝዌላ፣ በቻይና፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በሩሲያና በዩክሬን ላይ የሚከተለውን ፖሊሲ በዝርዝር ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ዘጋቢያችን ሲንዲ ሴይን ባጠናቀረችው ዘገባ መሠረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሩሲያን የሰሞኑን ውሣኔ አስመልክቶ ሲጠየቁ በሁለቱ ሃገሮች መካከል ያለው ግንኙነት መጥፎ እንደነበረና እንዲያውም የባሰም የተበላሸ ሊሆን እንደሚችል ለሩሲያው አቻቸው ሰርጌይ ላቭሮቭ ሲያሳስቡ እንደቆዩ፣ ያ የፈሩት ሁሉ አሁን መድረሱን አመልክተዋል።

በቲለርሰን እምነት ኮንግረሱ ባለፈው ሣምንት ያሣለፈውና ፕሬዚዳንት ትረምፕ ዛሬ ሕግ እንዲሆን የፈረሙበት የማዕቀቦች ውሣኔ ለሁለቱ ሃገሮች ግንኙነት መሻሻል አያግዙም።

“ኮንግረሱ በወሰደው ማዕቀቦቹን የመጣል እርምጃ ፕሬዚዳንቱም ሆኑ እኔ አልተደሰትንበትም” ሲሉ ቅሬታቸውን የገለፁት ሚስተር ቲለርሰን[ማዕቀቦቹ] “ለጥረቶቻችን ድጋፍ ይሰጣሉ ብለን እንደማናስብ በግልፅ ተናግረናል፤ እንደራሴዎቻችን ግን ውሣኔአቸውን አሳልፈዋል” ሲሉ አክለዋል።

ባይደሰቱበትም ግን ፕሬዚዳንቱም እርሣቸውም ለተፈፃማነቱ እንደሚሠሩ ቲለርሰን አመልክተዋል።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

ትረምፕ የሩሲያን ማዕቀብ ፈረሙ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:05 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG