በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሩሲያ የአሜሪካዊውን ጋዜጠኛ የእስር ጊዜ አራዘመች


ፎቶ ፋይል፦ ጋዜጠኛ ኢቫን ጌርሽኮቪች በሞስኮ ፍርድ ቤት እአአ መጋቢት 14/2023
ፎቶ ፋይል፦ ጋዜጠኛ ኢቫን ጌርሽኮቪች በሞስኮ ፍርድ ቤት እአአ መጋቢት 14/2023

የሩሲያ ፍርድ ቤት ከአንድ ዓመት በፊት በስለላ ወንጀል ተከሶ ያለ ፍርድ በቁጥጥር ስር የሚገኘውን አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ኢቫን ጌርሽኮቪች ፍርድ ቤት የሚቀርብበትን ጊዜ አራዝሟል። በጋዜጠኛው ላይ የቀረበውን ክስ ብዙዎች የሐሰት ውንጀላ ብለውታል።

ዛሬ ማክሰኞ ፍርድ ቤቱ ገርሽኮቪች ቢያንስ እስከ ሰኔ 30 ድረስ በእስር እንዲቆይ ያዘዘ ሲሆን ይህም ቀደም ሲል የተሰጠውን ትዕዛዝ በሦስት ወራት እንዲራዘም አድርጓል።

ሞስኮ ከሚገኘው ፍርድ ቤት ደጃፍ መግለጫ የሰጡት በሩስያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊን ትሬሲ ውሳኔውን አውግዘዋል።

"ኢቫን የጋዜጠኝነት ሥራውን በመስራቱ ብቻ ያለምንም ጥፋት ተይዞ ያካተሪንበርግ ከተማ ከታሰረ በዚህ ሳምንት አንድ ዓመት ሆኖታል፥ የእስር ጊዚው ይበልጥ እንዲራዘም መደረጉ ያማል" ብለዋል።

አምባሳደሯ አክለውም "የኢቫን ጉዳይ የማስረጃ፣ የፍትህ ሂደት ወይም የህግ የበላይነት አይደለም፡፡ የአሜሪካ ዜጎችን የፖለቲካ ዓላማን ለማሳካት መያዣ የማድረግ ጉዳይ ነው" ብለዋል።

ጌርሽኮቪች ችሎት የሚቀርብበት ቀን አልተወሰነም። የ32 አመቱ ጋዜጠኛ በቁጥጥር ስር የዋለው እአአ በመጋቢት 2023 በሩሲያ ካተሪንበርግ ከተማ ለዘገባ በመጓዝ ላይ እንዳለ ነው።

ጌርሽኮቪች እና ይሰራበት የነበረው ጋዜጣ የሩሲያን የስለላ ውንጀላ ውድቅ አድርገዋል። ሩሲያም ክሷን የሚደግፍ ማስረጃ አላቀረበችም።

ጋዜጣው ጌርሽኮቪች እንዲፈታ የሚካሄደውን ዘመቻ የሚያስተባብረው ረዳት አዘጋጁ ፖል ቤኬት ባለፈው ሳምንት ለቪኦኤ በሰጠው መግለጫ “ጌርሽኮቪች ንፁህ ሰው ነው፣ የአሜሪካ መንግሥት አስለቅቆ ወደ ቤቱ እንዲያስመልሰው እንጠብቃለን” ብሏል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጌርሽኮቪች በግፍ የተያዘ ነው ሲል አስታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG