በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሩቢዮ የስደተኞች እና የፀጥታ ጉዳዮች ላይ በተነጣጠረው የላቲን አሜሪካ ጉዟቸው ወደ ኮስታሪካ እና ጓቴማላ አቅንተዋል


የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማርኮ ሩቢዮ ከኢልሳልቫዶሩ ፕሬዝዳንት ናይብ ቡኬሌ ጋር በኤልሳልቫዶር እአአ የካቲት 3/2025
የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማርኮ ሩቢዮ ከኢልሳልቫዶሩ ፕሬዝዳንት ናይብ ቡኬሌ ጋር በኤልሳልቫዶር እአአ የካቲት 3/2025

የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማርኮ ሩቢዮ ፍልሰትን፣ በፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ የሚደረጉ ትብብሮች እና ቻይና በአካባቢው ላይ ያላትን ተጽእኖ ለመቋቋም የታለመውን የላቲን አሜሪካ ጉዟቸውን በመቀጠል፣ ዛሬ ማክሰኞ ከኮስታሪካ እና ዘግይቶም ከጓቲማላ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው ይነጋገራሉ።

ትላንት ሰኞ ከኢልሳልቫዶሩ ፕሬዝዳንት ናይብ ቡኬሌ ጋር ተገናኝተው የተነጋገሩት ሩብዮ፤ ከዩናይትድ ስቴትስ እንዲወጡ የሚደረጉት ሰዎች ዜግነት ምንም ይሁን ምን እንደሚቀበሉ ቡከሌ የገለጹላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

"የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች ወይም ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው ነዋሪዎች ቢሆኑም፤ በፈጸሙት ወንጀል የተነሳ በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙ አደገኛ ወንጀለኞችንም በተመሳሳይ ለመቀበል ፍቃደኝነታቸውን ገልጸዋል" ሲሉ ሩቢዮ አመልክተዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መሠረት የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የአሜሪካ ዜጎችን ከሀገር ማስወጣት አይችልም።

ኤል ሳልቫዶር በሕገ-ወጥ መንገድ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኙት ዜጎቿን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ሙሉ በሙሉ የምትተባበር መሆኗን የገለጹት ሩቢዮ አክለውም፤ ከኢልሳቫዶር ጋር የደረሱትን ስምምነት “ከፍልሰት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ ከአሁን ቀደም ተደርሶ የማያውቅ፣ በዓለም ፈጽሞ ያልታየ ስምምነት” ሲሉ አወድሰውታል። ቡከሌ በበኩላቸው ኤክስ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ መንግስታቸው ዩናይትድ ስቴትስ “የኢልሳልቫዶርን ማረሚያ ተቋማት በከፊል እንድትጠቀም መፍቀዷን” እንዲሁም የተፈረደባቸውን አደገኛ ወንጀለኞችን ተረክበው፣ የአሸባሪዎች ጥብቅ ማቆያ ማእከል በሆነው እጅግ ግዙፍ እስር ቤታቸው ውስጥ ለማቆየት መስማማቷን አመልክተዋል።

ኤልሳልቫዶር ለአገልግሎቱ የምትቀበለውም ክፍያ "በአንፃሩ ለዩናይትድ ስቴትስ በጣም ዝቅተኛ፤ ለእኛ ግን የማረሚያ ቤት ተቋማቶቻችንን ዘላቂ አቅም የሚያጎለብት ይሆናል" ብለዋል ቡከሌ። በሌላ በኩል ሩብዮ ‘የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ በምዕራቡ ንፍቀ ክበብ የሚያደርሰውን ተፅእኖ ለመከላከል፣ የሁለቱን ሀገራት እና የአከባቢውን ሉዓላዊነት እና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ስልቶችን በንግግራቸው አንስተዋል” ሲል የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ጨምሮ አስታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG