የባቡር መንገድ ኩባንያ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ ሊያደርጉ መነሳታቸው የሃገሪቱን የሸቀጥ ሥርጭት ያስተጓጉላል ያሚል ሥጋት እያየለ በመጣበት ወቅት፣ የባይደን አስተዳደር ኩባንያዎቹ እና የሠራተኛ ማኅበራቱ ጊዜያዊ ሥምምነት ማድረጋቸውን አስታወቀ።
ፕሬዚዳንት ባይደን ዛሬ ጠዋት እንዳስታወቁት የሠራተኛ ማኅበራቱና ኩባንያዎቹ የተሻለ ክፍያና የሥራ ሁኔታን በተመለከተ ሥምምነት ላይ በመድረሳቸው፣ በመላ ሃገሪቱ ሊደረግ የነበረው የሥራ ማቆም አድማ ተገቷል።
“ለባቡር መንገድ ሠራተኞቹ ድል ያስገኘ ሥምምነት ነው። እነዚህ ሠራተኞች በኮቪድ ወረሽኝ ወቅት አሜሪካውያን የሚያስፈልጋቸውን ነገር ቤታቸው ድረስ እንዲደርስ በማድረጋቸው አስቸጋሪ ዓመታትን እንድናልፍ ረድተውናል” ብለዋል ባይደን።
የሠራተኛ ጉዳዮች ምኒስትር ማርቲ ዋልሽ በትዊተር እንዳስታወቁት ሥምምነቱ የተደረሰው በሠራተኛ ማኅበራቱና በኩባንያዎቹ መካከል ለሃያ ሰዓታት ድርድር ከተደረገ በኋላ ነው። ሥምምነቱ የሠራተኞችን፣ የንግድ ድርጅቶችንና የሃገሪቱን የኢኮኖሚ ፍላጉት ያገናዘበ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
የተዘረጋው የባቡር መንገድ ሥርዓት ለአቅርቦት ሰንሰለቱ ወሳኝ በመሆኑ፣ መስተጓጎሉ በኢንዱስትሪዎች፣ ተጓዦችና በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ቤተሰቦች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያስከትል ነበር ሲሉ አክለዋል ዋልሽ።
የሰራተኛ ማኅበራቱ የተሻለ ክፍያና የሥራ ሁኔታን እንዲሁም የሃኪም ቀጠሮ የመሰሉ ጉዳዮችን ለማከናውን እንዲችሉ የተሻለ የሥራ ፈረቃ እንዲኖራቸው ጠይቀው ነበር።
ግዚያዊ ሥምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን የማኅበራቱ ዓባላት ማጽደቅ እንዳለባቸው ታውቋል።