በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትራምፕ ላይ ተቃውሞዎች እየተካሄዱ ነው


ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ
ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የዩናይትድ ስቴትስ አርባ አምስተኛው ፕሬዚዳንት ለመሆን የፊታችን ዓርብ ቃለ-መሃላ በሚፈፅሙት ተመራጭ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ የተቃውሞ ሣምንት ተጀምሯል።

ዋሺንግተን ዲሲ ውስጥ በሚገኝ አንድ ታሪካዊ ቤተ ክርስትያን ውስጥ በተካሄደ ሥነ-ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የሜሪላንድ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ክሪስ ቫን ሃለን “ዶናልድ ትራምፕ የነፃነት ኃውልትን እንዲቀብሩ አንፈቅድላቸውም” ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የሲቪል መብቶች ታጋይና ተሟጋቹ አል ሻርፕተን እዚያው ዋሺንግተን ዲሲ ውስጥ “አንገፋም” በሚል የተሰየመ ሰልፍ መርተዋል።

የቺካጎና አካባቢዋ የእሥላማዊ ድርጅቶች ምክር ቤት መሥራቹ ባሳም ኦስማን ደግሞ በሞቀ ድጋፍ ለተቀበሏቸው ሙስሊም ምዕመናን በፀሎት መክፈቻ ላይ ንግግር ባደረጉበት ወቅት “ጌታ ሆይ፤ ይህቺ ምድር ያንተ ምድር ናት፤ የትራምፕ ምድር አይደለችም” ብለዋል።

ሎስ አንጀለስ ከተማ ውስጥ ደግሞ የፍቅርና እንክብካቤ የፍልሰተኞች መብቶች ጥምረት የሚባል ድርጅት ቃል አቀባይ ሆርሄ ማሪዮ ካብሬራ “ትራምፕ ማኅበረሰባችንን ሲያጠፉ እጆቻችንን አጣጥፈን እንደማንቀመጥ ለአስተዳደራቸው ማሳሰቢያ እናስተላልፋለን” ብለዋል።

የቬርሞንቱ ሴናተር በርኒ ሳንደርስም ተመራጩ ፕሬዚዳንት ‘እሠርዘዋለሁ’ እያሉ ያሉትን “ለአቅም ተመጣጣኝ” በሚል መጠሪያ የሚታወቀውን የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን የጤና ጥበቃ አገልግሎት ዋስትና ሕግ እንዳይነኩ የሚጠይቁ ሰልፎችን እያስተባበሩና እየመሩ ናቸው።

ሚስተር ትራምፕ የፊታችን ዓርብ ቃለ-መሃላ በፈፀሙ ማግስት ከመላ ዩናይትድ ስቴትስ የሚሰበሰቡ ሁለት መቶ ሺኽ የሚሆኑ ሴቶች በአስተዳደራቸው ላይ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚወጡ ታውቋል።

XS
SM
MD
LG