በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሚሺጋን ፕሬዚደንታዊ ቅድመ ምርጫዎች ባይደን እና ትረምፕ አሸነፉ


መራጩ በሚሺጋን በድምጽ መስጫ ሥፍራ በዲትሮይት፤ ሚሺጋን
መራጩ በሚሺጋን በድምጽ መስጫ ሥፍራ በዲትሮይት፤ ሚሺጋን

በዩናይትድ ስቴትስ ሚሺጋን ክፍለ ግዛት ትናንት ማክሰኞ በተካሄዱት የሪፐብሊካን ፓርቲው እና የዲሞክራቲክ ፓርቲው ቅድመ ምርጫዎች ፕሬዚደንት ጆ ባይደን እና የቀድሞው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ አሸንፈዋል፡፡


ሁለቱም የየፓርቲያቸውን ቅድመ ምርጫዎች እንደሚያሸንፉ አስቀድሞም የተጠበቀ ቢሆንም በቅድመ ምርጫው የሚያገኙት ድምጽ መጠን በፕሬዚደንታዊ ምርጫው ቁልፍ በሆነችው በሚሺጋን ሁለቱ ተፎካካሪዎች ምን ያህል ድጋፍ እንዳላቸው የሚጠቁም በመሆኑ የትናንቱ ሂደት ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡


በዲሞክራቲክ ፓርቲው ቅድመ ምርጫ የተሰጡት ድምጾች ዛሬ ረቡዕ ማለዳ አብዛኛው ተቆጥሮ ፕሬዚደንት ፕሬዚደንት ባይደን 81 ከመቶ ድምጽ ያገኙ ሲሆን 13 ከመቶ ድምጽ ሰጪዎች ማንን እንደሚመርጡ እንዳልወሰኑ አሳይተዋል፡፡


በዩናይትድ ስቴትስ በአረብ አሜሪካውያን ብዛት ሚሺጋን አንደኛ ስትሆን አንዳንድ ዲሞክራቶች ፕሬዚደንት ባይደን እስራኤል በጋዛ በሓማስ ታጣቂዎች ላይ የምታካሂደውን ጦርነት መደገፋቸውን በመቃወም መራጮች ለፕሬዚደንቱ ድምጽ ከመስጠት “ አልወሰንነም “ የሚለውን እንዲመርጡ ቅስቀሳ አካሂደዋል፡፡


ቅስቀሳውን ያካሄዱት ወገኖች ተስፋ ያደረጉት “ማንን እንደምንደግፍ አልወሰንም” የሚለውን የሚመርጡ አስር ሺህ መራጮችን እናገኛለን ብለው ነበር፡፡ ሆኖም ቁጥሩ በቀላሉ ከአንድ መቶ ሺህ አልፏል፡፡


በሪፐብሊካን ፓርቲው ቅድመ ምርጫ ደግሞ ዛሬ ማለዳ የሚበዛው ድምጽ ተቆጥሮ ትረምፕ 68 ከመቶ የመራጭ ድምጽ ሲያገኙ ተፎካካሪያቸው የቀድሞዋ የደቡብ ካሮላይና አገረ ገዢ ኒኪ ሄሊ 27 ከመቶ ገደማውን አግኝተዋል፡፡ ትረምፕ እአአ በ2016 ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ሁለቱ ፓርቲዎች ብርቱ ፉክክር የሚያደርጉባት የሆነችውን ሚሺጋንን ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡ በ2020 ዓመተ ምሕረቱ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ግን ጆ ባይደን ሚሺጋን ላይ እንዳሸነፏቸው እና ያም ዳግመኛ ለመመረጥ ያደረጉት እንዲሰናከል መርዳቱ አይዘነጋም፡፡


ኒኪ ሄሊ እስካሁን ቅድመ ምርጫ ባካሄዱ ክፍለ ግዛቶች ቢሸነፉም ከፉክክሩ አልወጡም፡፡ አሜሪካውያን መራጮች የትረምፕ እና ባይደን ድጋሚ ውድድር አይፈልጉም በማለት የሚከራከሩት ሄሊ ያ ከሆነ ትረምፕ እንደገና በባይደን ይሸነፋሉ ብለዋል፡፡ ሄሊ ቢያንስ “ሱፐር ቲዩስዴይ” ተብሎ የሚጠራው አስራ አምስት ክፍለ ግዛቶች እና ዩናይትድ ስቴትስ የምታስተዳድራቸው ሁለት ግዛቶች ቅድመ ምርጫ እአአ መጋቢት 5 ድረስ መታገላቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡ ሪፐብሊካኖች በሐምሌ ወር ዲሞክራቶች ደግሞ በነሐሴ ወር ፕሬዚደንታዊ ዕጩዎቻቸውን ይመርጣሉ፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG