ትላንት ሌሊት በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞት፣ የዘረፋ ተግባርና ብጥብጥ ተካሂዷል።ጆርጅ ፍሎየድ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለ ሂወቱ ማለፉን በመቃወም ነው ግጭት አከል ሁከት የተከሄደው።
የፖሊስ መኪኖችና የመንግስት ህንጻዎች በእሳት ጋይተዋል። የሱቆች መስኮቶች ተሰባብረዋል፣ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ እቃዎች ተዘርፈዋል። በመናፈሻ ቦታዎች ያሉ ሀውልቶች በቀለሞች ተቀብተዋል። ተበላሽተዋል። ሰላማዊ የነበሩት የተቃውሞ ሰልፎች፣ ሁከት አዘል ሆነዋል።
የሚኒሶታና የ 11 ሌሎች ከፍላተ-ግዛት አስተዳዳሪዎች ጆርጅ ፍሎየድ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለ ሂወቱ ማለፉን በመቃወም የሚካሄዱትን ጥቃት አዘል ተቃውሞዎችን ለመግታት የብሄራዊ ዘብ ወታደሮችን አሰልፈዋል።
ካለፉት 4 ሌሊቶች ወዲህ ሲካሄዱ የቆዩት የተቃውሞ ስልፎች፣ መጀመርያ ላይ ሰላማዊ የነበሩ ቢሆንም፣ በሚንያፖሊስና በመንትየዋ ከተማ ሴንት ፖል እንዲሁም በሌሎች በሀገሪቱ ዙርያ ባሉት ከተሞች ወደ ዝርፊያ፣ ህንጻዎችንና ሌሎች ንብረቶችን ወደ ማጋየት እንዲሁም ወደ ሌሎች የግጭት ተግባሮች አምርተዋል።
“ወረራ እየተፈጸመብን ነው” ብለዋል የሚኒሶታ አስተዳዳሪ ቲም ዎልዝ። ህግንና ስርአትን ለማስከበር ሙሉ ሀይል እንጠቀማለን ሲሉም አክለዋል።
የጆርጂያ፣ የኬንታኪ፣ የኦሃዮ፣ የዊስካንሰን፣የኮሎራዶ፣ የዩታ፣ የዋሽንግተን፣ የካላኢፎርኒያ፡ የቴነሲ፣ የሚዙሪና የቴክሳስ ፍልተ-ግዛት አስተዳዳሪዎችም፣ ግጭት አከል የሆነውን ተቃውሞ ለመግታት ሲሉ፣ የብሄራዊ ዘብ ወታደሮችን አንቀሳቅሰዋል።
አሶሼትድ ፕረስ የዜና አገልግሎት ትላንት ቅዳሜ በዘገበው መሰረት፣ በሃገሪቱ ዙርያ ወደ 1,400 የሚሆኑ ሰዎች ታስረዋል። ትላንት ሌሊት ተቃውመው ስለቀጠለም፣ የታሰሩት ሰዎች ቁጥር ከዛ በላይም ሊሆን ይችላል።
በሀገሪቱ ዙርያ ያሉት ከንቲባዎች የሌሊት ሰአት እላፊ ገደብ ደንግገዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕረዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትላንት ስለ ፍሎይድ ህልፈት ሲናገሩ የጆርጅ ፍሎየድ በሚኒሶታ መንግዶች መሞት በጣም ያሳዝናል። መሆን አልነበረበትም። በመላ ሀገሪቱ ያሉትን አሜሪካውያን አሳዝኗል፣ አስቆጥቷልም” ብለዋል።
አያይዝውም ፕረዚዳንቱ፣ “እንደ ወዳጅና እንዳ አጋር ሆኜ ፣ ፍትህና ሰላም ከሚፈልጉት አሜሪካውያን ጎን እቆማለሁ። ይህን አሳዛኝ ክስተትን ተጠቅመው የሚዘርፉትንና ጥቃት የሚያደርቱትን ወገኖች በመቃወምም ከጎናችሁ እቆማለሁ” በማለት አስገንዝበዋል።
አሁን ያለው ተልእኮ ጥላቻ ሳይህን ፈውስ ማውረድ፣ ረብሻ ሳይሆን ፍትህ ነው ሲሉም ፕረዚዳንቱ አክለዋል።