የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ቢያንስ እስከፊታችን ሐሙስ፤ ካለበለዚያም ለመጭ በርካታ ቀናትና ሣምንታትም በከፊል ዝግ እንደሚሆን ተገልጿል።
የመንግሥቱ ከፊል መዘጋት ምክንያት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ከጠየቁት ሃገሪቱ ከሜክሲኮ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ላይ የግንብ አጥር ለማቆም የሚያስችል ወጭ ያካተተ በጀት አለማፈግፈጋቸው እና ዴሞክራቱ እንደራሴዎች ደግሞ ግንብ የማቆም ሃሣብን በፅኑ መቃወማቸውን መቀጠላቸው ነው።
ፕሬዚዳንቱ ዛሬ ባወጡት የትዊተር መልዕክት “ዴሞክራቶቹ ቀደም ባሉ ጊዜያት ይዘውት በነበረ አቋም በድንበሩ ላይ የግንብ ወይም የአጥር ቋሚ መከለያ እንዲኖር አጥብቀው ሲደግፉ ቆይተዋል” ብለዋል። ሃሣቡን የተቃወሙት የእርሣቸው የምረጡኝ ዘመቻ ማዕከላዊ ጉዳይ ከሆነ በኋላ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የሕግ ወመሰኛ ምክር ቤቱ ሁለተኛ ዴሞክራት አባል የኢሊኖዩ ዲክ ደርቢን ከትናንት በስተያ ቅዳሜ በትዊተር ባሰራጩት ቃል “ትረምፕ መንግሥቱን ለመዝጋት የወሰኑት ኋላ ቀር ለሆነ የመካከለኛ ዘመን የወሰን ላይ ግንብ ሲሉ ነው፤ ትርጉም የለሽና የጭካኔ እርምጃ” ብለዋል።
የተወካዮች ምክር ቤቱና ዋይት ሃውስ ቤተመንግሥት በበጀት ጉዳይ ላይ ባለመስማማት መንግሥቱን በከፊል ወደመዝጋት ሲሄዱ ባለፉ አምስት ዓመታት ውስጥ የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑ ነው።
ባለፈው ሃሙስ በሪፐብሊካኑ አብላጫ የተያዘው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ዋይት ሃውስ እንደሚቀበለው ፍንጭ ያሳየበትን እስከፊታችን የካቲት የሚያደርስ ጊዜያዊ የወጭ ሕግ በአንድ ድምፅ ሲያፀድቅ የመንግሥቱ መዘጋት ሊቀር ይችላል የሚል ተስፋ አሣድሮ የነበረ ቢሆንም ዘግየት ብሎ ግን ፕሬዚዳንት ትረምፕ ቀደም ሲል የጠየቁት የ5.7 ቢሊዮን ዶላር የግንብ ወጭ ጥያቄ ላይ የሙጥኝ በማለታቸው ከትንናንት በስተያ ዕኩለ ሌሊት ላይ ቀነ-ገደቡ ሲልፍ መንግሥቱ በከፊል ተዘግቷል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ