ዩናይትድ ስቴትስ፣ በወታደራዊ ኃይል ቁጥጥር ሥር ለምትገኘው ኒዤር የምትሰጠውን፣ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ርዳታ እንዳቋረጠች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ማት ሚለር እንዳስረዱት፣ እንዲቋረጥ የተደረገው ርዳታ፣ ለጸጥታ ጥበቃ እና ለልማት ይውል የነበረውን ብቻ እንጂ፣ ለኒዤር ሕዝብ የሚሰጠውን የሰብአዊ ርዳታ አያካትትም።
የርዳታው መጠን “ከፍተኛ” ነው፤ ያሉት ሚለር አክለውም፣ "የወታደራዊው ጁንታ መሪዎች፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዐቱ እንዲመለስ አድርገው ዘወር ቢሉ፣ ለጸጥታ ጥበቃ ይሰጥ የነበረውና የተቋረጠው ይኸው ርዳታ፣ ወዲያውኑ እንዲቀጥል ይደረጋል፤” ብለዋል። “በግልጽ እንዳስቀመጥነው፣ ያ ባልኾነበት ግን፣ በመቶ ሚሊዮን ዶላር የሚሰላው የርዳታ ገንዘብ፣ ዕጣ ፈንታው መቋረጥ ብቻ ነው፤" ሲሉ፣ ቃል አቀባዩ አብራርተዋል።
ሚለር፣ ትላንት ሰኞ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት፣ በኃይል ከሥልጣናቸው የተወገዱትን፣ የኒዤር የቀድሞ ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዙምን፣ ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ እንዳነጋገሯቸውና በዚያች አገር እየኾነ ያለውን ኹኔታ አስመልክቶም፣ ከሌሎች ቁልፍ የአፍሪካ እና የአውሮፓ መሪዎች ጋራ፣ በስልክ መነጋገራቸውን አመልክተዋል።
በተያያዘ ዜና፣ በግል ስላደረጓቸው ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች፣ አስተያየት ለመስጠት የፈቀዱና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት እንደገለጹት፣ የባይደን አስተዳደር፣ በኒዤር የተፈጸመው ድርጊት፣ ከመፈንቅለ መንግሥት የሚመደብ መኾን አለመኾኑን፣ አሁንም በመገምገም ላይ ይገኛል።
ለኒዤር ወታደራዊ መሪዎች፣ የያዙትን የኃይል መንገድ ለመቀልበስ እና ሥርዐት እንዲሰፍን ለማድረግ፣ “አሁንም አልመሸም” ሲሉ፣ ባለሥልጣናቱ አክለዋል።
መድረክ / ፎረም