በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ ለአፍጋኒስታን ድጋፏን እንደምትቀጥል አስታወቀች


ዩናይትድ ስቴትስ በታሊባን ጥቃት ለተከፈተባቸው የአፍጋኒስታን ወታደሮች በአየር ጥቃት ድጋፏን እንደምትቀጥል አስታወቀች።

ዩናይትድ ስቴትስ የታሊባን ታጣቂዎች ጥቃት የከፈቱባትቸውን የአፍጋኒስታን ወታደሮች ለመርዳት በታጣቂዎቹ ላይ የአየር ድብደባ ማካሄዷን እንደምትቀጥል ትናንት አንድ በክልሉ ያሉ የዩናይትድ ስቴትስ አዛዥ አስታውቀዋል።

አፍጋኒስታን የነበሩት አብዛኞቹ የዩናይትድ ስቴትስ እና ዓለም አቀፍ ሃይሎች ወታደሮች ወጥተዋል። ባለፈው ሚያዚያ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን አሜሪካውያኑ ወታደሮች እንደሚወጡ ማስታወቃቸውን ተከትሎ ባለፉት ሳምንታት ጥቃቱን እያፋፋመ ያለው ታሊባን የገጠር ወረዳዎችን ተቆጣጥሯል፤ የክፍለ ሃገር ዋና ከተሞችንም ከብቧል።

የዩናይትድ ስቴትስ ጄኔራል ኬኔት ፍራንክ ሜኬንዚ ካቡል ውስጥ በተካሄደ ጋዜጣዊ ጉባኤ "ዩናይትድ ስቴትስ ባለፉት በርካታ ቀናት ለአፍጋን ኃይሎች በአየር ሃይል የምትሰጠውን ድጋፍ አጠናክራለች፥ በቀጣዮቹ ሳምንታትም ታሊባን ጥቃት ማካሄዱን ሲቀጥል እኛም በዚሁ በተጠናከረ ደረጃ ለአፍጋን ሃይሎች በአየር ጥቃት ድጋፍ መስጠታችንን እንቀጥላለን ብለዋል።

አፍጋኒስታንን ጨምሮ በሌሎችም የአካባቢው ሃገሮች ያሉ የዩናይትድ ስቴትስ ኃይሎችን የሚጨምረው የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ሰራዊት ማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ የሆኑት ጄኔራል ሚከንዚ የዩናይትድ ስቴትስ ኃይሎች ተልዕኮአቸው እአአ ነሃሴ 31 ከተጠናቀቀ በኋላም የአየር ጥቃቱ ይቀጥል እንደሆን በግልጽ ከመናገር ተቆጥበዋል።

የአፍጋኒስታን መንግሥት በመጪዎቹ ቀናት ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል ያሉት ጄኔራሉ ታሊባኖቹ የጥቃት ዘመቻቸው እንደማይቆም ለማሳወቅ እየሞከሩ ናቸው። የሆኖ የነሱ ድል አድራጊነት አይቀሬ አይደለም፥ አሁንም ቢሆን ለግጭቱ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማግኘት ዕድል አለ ብለዋል።

የአፍጋኒስታን መንግሥት እና የታሊባን ተደራዳሪዎች በቅርብ ሳምንታት ካታር መዲና ዶሃ ላይ ስብሰባዎች አካሂደዋል። ዲፕሎማቶች እንደሚሉት ግን የሰላም ድርድራቸው በመስከረም ወር ከተጀመረ ወዲህ ብዙም እርምጃ አልተመዘገበም።

XS
SM
MD
LG