በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አሜሪካ ከኒዠር ለመውጣት ድምዳሜ ላይ አለመድረሷን አስታወቀች


ፎቶ ፋይል፦ የኒዠር ወታደራዊ መሪዎች በጄኔራል ሴይኒ ኩንቼ ስታዲየም ለደጋፊዎቻቸው ሰላምታ እየሰጡ፤ ኒያሜ፣ ኒዠር እአአ ነሃሴ 26/2023
ፎቶ ፋይል፦ የኒዠር ወታደራዊ መሪዎች በጄኔራል ሴይኒ ኩንቼ ስታዲየም ለደጋፊዎቻቸው ሰላምታ እየሰጡ፤ ኒያሜ፣ ኒዠር እአአ ነሃሴ 26/2023

የኒዠር ወታደራዊ አገዛዝ የአሜሪካ ወታደሮች ሀገሪቱ ሰፍረው በጸረ ሽብርተኛ እንቅስቃሴዎች እንዲሳተፉ የፈቀደውን ስምምነት ሰርዘናል ብሎ ቢያስታውቅም ዩናይትድ ስቴትስ "መውጣታችን ነው" የሚል ድምዳሜ ላይ እንዳልደረሰች አመልክታለች።

ትናንት ሰኞ የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚንስቴር ባለሥልጣናት በሰጡት ቃል "ኒዠር ካሉን 1000 የሚሆኑ ወታደራዊ አባላት እስካሁን አንድም አላስወጣንም" ብለዋል። ኋይት ሀውስ እና የዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴርም በበኩላቸው ከኒዠር ባለሥልጣናት ጋራ ንግግሩ እንደቀጠለ መሆኑን አመልክተዋል።

የኒዠር ወታደራዊ አገዛዝ ቃል አቀባይ ባለፈው ቅዳሜ በሰጡት መግለጫ የዩናይትድ ስቴትስ ኃይሎች ከኒዠር የጦር ኃይል ጋር በጸረ ሽብርተኛ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በትብብር እንዲንቀሳቀሱ የፈቀደውን ስምምነት ሰርዘናል ሲሉ አስታውቀዋል።

ቃል አቀባዩ ኮሎኔል አማዱ አብድራማኒ ውሳኔው ላይ የተደረሰው ባለፈው ሳምንት በኒያሜ ከኒዠር ባለሥልጣናት ጋር የተገናኙት ከፍተኛ የዩናይትድ ስቴትስ ልዑካን ያሳዩት " የንቀት አስተያየት" ባሉት ምክንያትም ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል ።

ባለፈው ሳምንት ኒያሜን የጎበኙት የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ረዳት ሚንስትር ሞሊ ፊ ፣ የመከላከያ ሚንስቴር ረዳት ሚኒስትር ሰለስት ዋላንደር እና የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ኃይል የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጀኔራል ማይክል ላንግሊ ያደረጉት ውይይት ግልጽና ቀጥተኛ እንደነበረ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ገልጸዋል። ልዑካኑ ዩናይትድ ስቴትስ ያላትን ስጋት የገለጹ ሲሆን የኒዠር ወታደራዊ እና ሲቪል ባለሥልጣናትን ሀሳቦችም አድምጠዋል ብለዋል።

ኢራን ባለፈው ጥር ወር የኒዠር ጠቅላይ ሚንስትር አሊ ማሃማን ላሚን ዚኒን ተቀብላ ያስተናገደች ሲሆን ሀገራቸው መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎ የተጣለባትን ዓለም አቀፍ ማዕቀብ እንድትቋቋም ልትረዳ ቃል መግባቷን ዘገባው አያይዞ ጠቅሷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG