አሜሪካ ውስጥ በመወለድ ዜግነት የሚያሰጠው ሕግ፣ ያለ ሕጋዊ ፈቃድ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በገቡ ሰዎች ለተወለዱ ልጆች ተፈጻሚ እንዳይሆን የሚያደርገውን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የፈረሙትን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ በማገድ የኒው ሃምፕሸር ክፍለ ግዛቱ የፌዴራል ዳኛ ጆሴፍ ኤን ላፕላንት በትላንትናው ዕለት በሰጡት ብይን ሦስተኛው ዳኛ ሆኑ።
በዩናይትድ ስቴትስ የሲቪል መብት ማሕበራት ባቀረቧቸው ክሶች፤ ትረምፕ የፈረሙትን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ሕገ መንግስቱን የሚጥስ እና "ከዋነኞቹ የአሜሪካ ሕገ-መንግሥታዊ እሴቶች ውስጥ አንዱን ለመለወጥ የተደረገ ሙከራ ነው” ሲሉ ተከራክረዋል።
‘አሜሪካን ሲቪል ሊበሪቲ ዩንየን’ የተባለው የዩናይትድ ስቴትሱ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ‘የኢሚግሬሽን መብቶች ጉዳይ’ ምክትል ድሬክተር ኮዲ ዋፍሲ ሲናገሩ፡ "ይህ በሕገ መንግስቱ ውስጥ ያለ እና እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1868 ከፕሬዝዳንቱ የማዘዝ ሥልጣን ውጭ እንዲሆን የተደረገ ነው። እንዳሻን ልንሟገት እንችላለን። ይሁን እንጂ ሕጉ አያወላዳም። እርምጃው ኢ-ሕገ መንግስታዊ እና ሕገ-ወጥ ነው” ብለዋል።
ዳኛው ላፕላንት "ፕሬዝዳንታዊው ትዕዛዝ ተገቢ ነው" ሲል የትረምፕ አስተዳደር ያቀረበውን መከላከያ "አሳማኝ ሆኖ አላገኘሁትም’ ብለዋል።
አስተያየታቸውን የተጠየቁ የአስተዳደሩ ጠበቆች ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል። ሆኖም የትረምፕ ሪፐብሊካን አስተዳደር የአሜሪካ ዜጋ ያልሆኑ ወላጆች የሚያፈሯቸው ልጆች ‘በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ሥልጣን ሥር የማይውሉ ወይም የማይገዙ" በመሆናቸው የዩናይትድ ስቴትስ ዜግነት መብትም የላቸውም ሲል ሞግታል።
ላፕላንት ያሳለፉት ብይን ባለፈው ሳምንት በሲያትል ዋሽንግተን እና በሜሪላንድ ክፍለ ግዛቶች ውስጥ ሁለት ዳኞች ተመሳሳይ ውሳኔዎችን ማሳለፋቸውን የተከተለ ነው።
መድረክ / ፎረም