ሄይቲ ውስጥ አስራ ሰባት አሜሪካዊ ሚሲዮናውያን በሽፍቶች መጠለፋቸው ተዘገበ። ከተጠለፉት መካከል ልጆችም ያሉባቸው መሆኑ ተገልጿል።
ሚሲዮናውያኑ መጠለፋቸውን የገለጸው ስለጉዳዩ መረጃ የደረሰው ሃይማኖታዊ ተቋም ባስተላለፈው መልዕክት መሆኑን ዜናው አመልክቷል።
ጽህፈት ቤቱ ዩናይትድ ስቴትስ ኦሃዮ ክፍለ ሃገር የሆነው ክሪስቲያናዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት የበጎ አድራጎት ድርጅት ለሌሎች መሰል ተቋማት ባስተላለፈው ጥሪ
"ጠላፊዎቹ በአድራጎታቸው ተጸጽተው ንስሃ እንዲገቡ እንጸልይላቸው" ሲል ተማጽኖ አቅርቧል።
ሚስዮናውያኑ የተጠለፉት በሄይቲ በዕጉዋለ ማውታን መኖሪያ ቤት ግንባታ ለመርዳት ሥራ ላይ ሳሉ ከስፍራው ወጣ እንዳሉ መሆኑን ነው መግለጫው የጠቆመው።
የመስክ ሃላፊው ስለጠለፋው የዩናይትድ ስቴትስን መንግሥት ማሳወቃቸው ተገልጿል። አንድ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ቃል አቀባይ ሪፖርቱ እንደደረሳቸው ገልጸዋል፥ የዜጎቻችንን ደህንነት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ቅድሚያ ትኩረት ይሰጣል ያሉት ቃል አቀባዩ ሌላ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።
በቅርቡ ሄዪቲን የጎበኙ ከፍተኛ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ባለሥልጣናት የሃገሪቱ ፖሊሶች በወንበዴ ቡድኖች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመቆጣጠር እንዲችሉ ለመርዳት ተጨማሪ አስራ አምስት ሚሊዮን ዶላር እንሰጣለን ሲሉ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።