አሜሪካ ወታደሮቿን ከኒጀር አስወጥታ ማጠናቀቋን አንድ ከፍተኛ የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣን ትላንት ሰኞ አስታውቀዋል፡
የፔንታገን ቃል አቀባይ የሆኑት ሳብሪና ሲንግ፣ በኒጀር የሚገኘውን የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ለመጠበቅ ጥቂት ወታደሮች ብቻ መቅረታቸውንም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
በአውሮፓዊያኑ 2024 መግቢያ ላይ፣ የኒጀር ወታደራዊ ጁንታ የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች በምዕራባዊቷ አፍሪካ ሃገር ያላቸውን ተልዕኮ የፈቀደውን ስምምነት እንዲያበቃ አድርጓል፡፡
የሁለቱ ሃገራት ባለሥልጣናት ከጥቂት ወራት በኋላ በጋራ ባወጡት መግለጫም፣ የአሜሪካ ወታደሮች በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ ሙሉ ለሙሉ ለቀው እንደሚወጡ ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ የመጨረሻውን የጦር ሰፈሯን ከአንድ ወር በፊት ለአካባቢው ባለስልጣናት ያስረከበች ሲሆን፤ ከ20 በላይ የሚሆኑ ወታደሮቿ ለቆ ከመውጣት ጋር ለተያያዙ የተለያዩ አስተዳደራዊ ስራዎች በሃገሪቱ ቀርተው ነበር ሲሉ ሲንግ አስታውቀዋል፡፡
ከቅርብ ወራት ወዲህ ኒጀር ከምዕራባዊያን አጋሮች በመራቅ፤ ለደህንነት ጉዳዮች ፊቷን ወደ ሩሲያ አዙራለች፡፡ የሩሲያ ወታደራዊ አሰልጣኞች የሃገሪቱን የአየር መከላከያ ሠራዊት ለማሰልጠን ባለፈው ሚያዚያ ኒጀር ገብተዋል፡፡
መድረክ / ፎረም