በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አል-ሻባብን በጦር “ብቻ ማሸነፍ አይቻልም”


ፎቶ ፋይል
ፎቶ ፋይል

አል-ሻባብን በጦር ሠራዊት ብቻ ማሸነፍ አይቻልም ሲሉ ሁለት የሶማሊያ የቀድሞ ሚኒስትሮች አሳስበዋል።

ከታጣቂዎቹ ጋር የሚደረጉ “የጦር ፍልሚያዎችና የዩናይትድ ስቴትስ የአየር ድብደባ ብቻቸውን አል-ሻባብን አያጠፉትም” ሲሉ በቀድሞው የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሃሰን ሼህ ሞሐመድ አስተዳደር ወቅት የደኅንነት ሚኒስትር የነበሩት አብዲራዛቅ ሞሐመድ ከአሜሪካ ድምፅ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አሳስበዋል።

“ቡድኑ ለረዥም ጊዜ መርዛም አስተሳሰብን በወጣቶችና ለቅስቀሳው ተጋላጭ በሆኑ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ውስጥ ሲዘራ የኖረ በመሆኑ ያንን በውጤታማ ሁኔታ ለማጥፋት ከመሪዎቹ ጋር ንግግር መጀመር አስፈላጊ ነው፤ ጦርነት ብቻውን አል-ሻባብን አያከስመውም” ብለዋል ሚኒስትሩ።

አብዲራዛቅ ሥራ ላይ በነበሩ ወቅት ይፋ ያልወጣና ያልተሣካ ንግግር ከአል-ሻባብ ጋር ጀምረው የነበረ ቢሆንም በራሣቸው አባባል መንግሥቱ ሥልጣን በመልቀቁ ምክንያት ጅምሩ ሳያልቅ መቅረቱን ተናግረዋል።

ከአል-ሻባብ ጋር ውይይት መጀመር የሽብር አድራጎቱን እስካላቆመና ጥቃት መፈፀሙን እስከቀጠለ ድረስ መዋጋቱ ይቁም ማለታቸው እንዳልሆነ የገለፁት የቀድሞው የደኅንነት ሚኒስትር “በንግግር አዲስ የመፍትኄ መንገድ መሞከር ግን ሁልጊዜም የሚቻል ነገር ነው” ብለው እንደሚያምኑ አመልክተዋል።

“በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስና በታሊባን መካከል በቅርቡ የተጀመሩት የሰላም ንግግሮች ዕድገትና ተስፋ ማሳየታቸው ይታወቃል። ያንን ማድረግ ከተቻለ የአሁኑ የሶማሊያ መንግሥትም ከአልሻባብ ጋር የንግግር መድረክ ማመቻቸት ይችላል” ብለዋል የቀድሞው የደኅንነት ሚኒስትር።

በሌላ በኩል የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ዕዝ አዣዥ ጄነራል ቶማስ ዋልድሃውዘር ለሃገራቸው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ያለ ሶማሊያ ጦር ድጋፍ በአሜሪካ ተከታታይ የአየር ድብደባ ብቻ ብዙ ውጤት ማስገኘት እንደማይቻል በመግለፅ ላስተላለፉት መልዕክት ትናንት ከቪኦኤ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ምላሽ የሰጡት የሶማሊያ የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር ጄነራል አብዱልቃዲር አሊ ዲኒም የሕዝብ ድጋፍን አስፈላጊነት አስረግጠው ተናግረዋል።

“ጦሩ የራሱን ሥራ ያከናውናል። ከፍተኛ አዛዦቹንና ወታደሮቹን ከአል-ሻባብ ጋር በሚያደርገው ውጊያ እያጣ ይቀጥላል። ይሁን እንጂ የሶማሊያ ሕዝብና ቁርጠኛነት ያላቸው ፖለቲከኞች እውነተኛ ድጋፍ ያጥረዋል” ብለዋል።

ከሃያ ሺህ በላይ ወታደሮች ያሉት የአፍሪካ ኅብረት ጦር ላለፉት ሁለት ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ የአየር ድብደባ እየታገዘ በአል-ሻባብ ላይ እያካሄደ ባለው ውጊያ በሺሆች የሚቆጠሩ ታጣቂዎችና ነፍሰ-ገዳዮችን ማስወገድ ቢችልም ቡድኑ በሃገሪቱና ከዚያም ውጭ ያሳደረውን ሥጋት ማጥፋት ግን አስቸጋሪ እንደሆነ መቀጠሉ ይነገራል።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ

አል-ሻባብን በጦር “ብቻ ማሸነፍ አይቻልም”
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:27 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG