በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የማይክል ፓክ ሹመት በሴኔቱ ኮሚቴ አለፈ


ፎቶ ፋይል፦ ማይክል ፓክ
ፎቶ ፋይል፦ ማይክል ፓክ

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የአሜሪካ ድምፅና ሌሎችም ዓለምአቀፍ የሥርጭት አውታሮችን በበላይነት የሚመራው የዩናይትድ ስቴትስ ዓለምአቀፍ ሚድያ ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ እንዲሆኑ ያጯቸውን የማይክል ፓክን ሹመት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ዛሬ አሳልፏል።

የኮሚቴው ውሣኔ ያለፈው 12 ለ 10 በሆነ የፓርቲ ወገን በለየ ድምፅ ሲሆን በሴኔቱ ውስጥ አብላጫ መቀመጫ ያላቸውና ኮሚቴውንም የሚቆጣጠሩት ሪፐብሊካን አባላት የይሁንታ ድምፅ ሲሰጡ ዴሞክራቶቹ ተቃውመዋል።

የዘጋቢ ፊልሞች ሠሪ የሆኑት ማይክል ፓክ የሹመት ጉዳይ ሁለት ዓመት ለሚሆን ጊዜ ሲጓተት የቆየ ሲሆን ከምክንያቶቹ አንዱም “በግል ሥራቸው ውስጥ እራሣቸውን ያለአግባብ ጠቅመዋል የሚል ክሥ አለባቸው” በሚል ዴሞክራቶቹ ሴናተሮች ያነሱት ሥጋት እንደሆነ ይታወቃል።

ባለፈው ሣምንትም የዋሺንግተን ዲሲ ዋና አቃቤ ሕግ ቢሮ “ፐብሊክ ሚድያ ላብ” ከሚባለው የተቋቋመው ለትርፍ ያልሆነ ድርጅት ገንዘብ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ አውጥተው ለግላቸው አውለው እንደሆነ እፈትሻለሁ በሚል ምርመራ በመክፈቱ ኮሚቴው ሊሰጥ የነበረው ድምፅ ተላልፏል።

ያንን መሸጋገር ተከትሎ ዋይት ሃውስ ተቃውሞ ያሰማ ሲሆን ፕሬዚዳንት ትረምፕ ፓክን እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

የዛሬውም ድምፅ ከመሰጠቱ በፊት የዋሺንግተን ዲሲው አቃቤ ሕግ ምርመራውን እስኪጨርስ የፓክ ሹመት ጉዳይ እንዲሸጋገር ዴሞክራቶቹ ሴናተሮች ያደረጓቸው በርካታ ጥረቶች ከሽፈዋል።

የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴው ከፍተኛ አባል የሆኑት ዴሞክራቱ ባብ ሜኔንዴዝ ባሰሙት ቅሬታ “ፓክ ከፍ ባሉ ጉዳዮች ላይ በቅን መንፈስ ሊያናግሩኝ ተስኗቸዋል፤ ገብተውባቸው የነበሩ ግዴታዎችን ሳይፈፅሙ ቀርተዋል” ሲሉ ወቅሰዋል። “በሪፐብሊካኖቹ የሚመራው ኮሚቴም የሹመቱን ሂደት ሁለቱንም ወገኖች ባሳተፈ ሁኔታ ማስኬድ ተስኖታል” ብለዋል።

የኮሚቴው ሊቀመንበር ጂም ራይሽ ግን የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት ሂደቱ እንዲዘገይ ቢጠይቅ ኖሮ ያዘገዩት እንደነበር ጠቁመው ያ ግን አለመሆኑን ተናግረዋል።

ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጠው ቪኦኤ ለሊቀመንበር ራይሽ ቃል አቀባይ ካቀረበው ጥያቄ ተነስተው ራይሽ በሰጡት ምላሽ ለብዙ ጊዜ ባዶ ሆኖ ለቆየው የዩኤስ ዓለምአቀፍ ሚድያ ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቦታ እንዲሟላ ኮሚቴው ለሚስተር ፓክ ሹመት ይሁንታ በመስጠቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።

“ሚስተር ፓክ የተቋቋመው ለትርፍ ባልሆነውና በአትራፊው ንግዳቸው መካከል ያለውን ግንኙነት ለሃገር ውስጥ ገቢ መሥሪያ ቤቱ በተሣሣተ ሁኔታ አቅርበዋል” ሲሉ ባብ ሜኔንዴዝ ክሣቸውን አብራርተዋል።

የሚስተር ፓክ ቃል አቀባይ ለተባለው ሁሉ መልስ እንዲሰጡ ቪኦኤ ጥያቄ አቅርቧል።

የዕጯቸው ሹመት ለሁለት ዓመታት መጓተቱ እንዳበሳጫቸው ፕሬዚዳንት ትረምፕ ሰሞኑን ተናግረው ነበር።

የዩናይትድ ስቴትስ ዓለምአቀፍ ሚድያ ኤጀንሲ (ዩ.ኤስ.ኤ.ጂ.ኤም.) በበላይነት የሚያስተዳድራቸው ዓለምአቀፍ ሲቪል የሥርጭት መረቦች ቪኦኤ፣ “ራዲዮ ሊበርቲ” ተብሎ የሚታወቀው ነፃዪቱ አውሮፓ ራዲዮ፣ የኩባ ብሮድካስቲንግ ቢሮ፣ ነፃ እስያ እንዲሁም በዓረብኛ የሚያሠራጩትን አልሁራ ቴሌቪዥንና ራዲዮ ሳዋን ያቀፈውን የመካከለኛው ምሥራቅ የሥርጭት መረቦችን ነው።

ሚስተር ፓክ ሹመታቸው ቢፀድቅ ቪኦኤን ጨምሮ ነፃና ሚዛናዊ ዘገባዎችን እንዲሠሩ ሕግ በሚያዝዛቸው ሌሎቹም የዩ.ኤስ.ኤ.ጂ.ኤም. የሥርጭት ተቋማት ላይ የፖለቲካ ጫና ያሳድሩ እንደሆነ ባለፈው መስከረም በኮሚቴው ፊት ተጠይቀው ነበር።

ፓክ ሲመልሱ “መላው ኤጀንሲ በሪፖርተሮቹ ነፃነት ላይ የተመሠረተ ነው፤ ዜናዎችን እንዴት መሥራት እንዳለባቸውና ምን ማለት እንዳለባቸው ማንም የፖለቲካ ጫና አይነግራቸውም፤ ያለዚያ መተማመን ኤጀንሲው ሙሉ በሙሉ ውድቅ የሚሆን ይመስለኛል” ብለዋል።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

የማይክል ፓክ ሹመት በሴኔቱ ኮሚቴ አለፈ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:52 0:00


XS
SM
MD
LG