ዩናይትድ ስቴትስ ሚሺጋን ስቴቷ ዲትሮይት ከተማ ውስጥ ሥራ የማቆም አድማ ከመቱ 13 ሺህ የሚሆኑ መኪና አምራች ሠራተኞች ጋር የግዛቲቱ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት እንደራሴዎች አብረው ተሰለፉ።
ሠራተኞቹ አድማ የመቱት የማኅበራት መሪዎቻቸው ከአሠሪዎች ጋር እስከ ትናንት፣ ሃሙስ እኩለ ሌሊት ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻላቸው ነው።
ዩናይትድ አውቶ ዎርከርስ ዩኒየን የሚባለው የሠራተኛ ማኅበር አባላት ኦቶሞቢል ከሚያመርቱት ጄኔራል ሞተርስ፣ ፎርድና ስቴላንቲስ ከፍ ያለ የደመወዝ ጭማሪና የተሻሉ ጥቅማጥቅሞችን መጠየቃቸው ተነግሯል።
ሠራተኞቹ ከዓመታት በፊት ፋብሪካዎቹ ኪሣራ ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ቀርቶባቸው የነበረው ክፍያ አሁን እንዲከፈላቸው እንደሚፈልጉ ታውቋል።
ሴኔተሮቹ ጌሪ ፒተርስና ዴቢ ስታቢናው ለሠራተኞቹ ድጋፋቸውን ለመግለፅ ዌን ከተማ ውስጥ አብረዋቸው ተሰልፈዋል።
በሚዙሪው የዌንትዝሚል የጀኔራል ሞተርስ መገጣጠሚያ፣ ሚሺጋን ውስጥ ዲትሮይት አቅራቢያ በምትገኘው ዌይን የፎርድ ፋብሪካና ቶሌዶ፣ ኦሃዮ ባለው የስቴላንቲስ ጂፕ መኪና ፋብሪካ ውስጥ ከሚሠሩትና የማኅበሩ አባላት ከሆኑት146 ሺህ ሠራተኞች የሥራ ቦታቸውን ረግጠው ለአድማ የወጡት እጅግ ጥቂቱ መሆናቸውን አሶሲየትድ ፕሬስ በዘገባው ጠቁሟል።
መድረክ / ፎረም