የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባስተላለፉት ትዕዛም ከትናንት በስቲያ አርብ እስከ እሁድ ድረስ በኮሮና ቫይረስ ምክኒያት ሕይወታቸው ለተቀጠፉ 100 ሺህ የሚጠጉ አሜሪካውያን መታሰቢያ እንዲሆን በሚል ለሦስት ቀናት የአሜሪካን ባንዲራ ዝቅ ብሎ ተውለብልቧል።
ዩናይትድ ስቴትስ የአርበኞች ጉዳዮች ሚኒስቴር በተገኘው መረጃ መሰረት 1 ሺሕ አርበኞች በኮሮና ቫይረስ ምክኒያት ሕይወታቸውን አጥተዋል። እነዚህን አርበኞች ጨምሮ 100 ሺሕ አሜሪካውያን በኮሮና ቫይረስ ምክኒያት ሕይወታቸውን በማጣታቸው ዩናይትድ ስቴትስ በሟቾች ቁጥር ከዓለም ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች።
ለአገራቸው የወደቁ ዜጎችን ለማሰብ በተሰኘመውና ብሔራዊ በዓል በሆነው የዛሬው ሰኞ “ሚሞሪያል ዴይ” ወትሮ ይፋዊ ያልሆነ የበጋ ወራት የሚጀመርበት ወቅት ነበር። ቤተሰቦች ለሽርሽር ወደ ባህር ዳርቻ ጎራ የሚሉበትና የሚዝናኑበት ጊዜም ነበር። ነገር ግን ዘንድሮ በኮሮና ቫይረስ ምክኒያት በተላለፈው አካላዊ ርቀትን የመጠበቅ መመሪያ ፣ወተለያዩ ቦታዎች የጉዝ እቀባ እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሥራ ማጣት ምክኒያት የዘንድሮው የመታሰቢያ ቀን ካለፉት ዓመታት የተለየ መልክ እንዲኖረው አድርጎታል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አርሊንግተን የሚገኘው ብሔራዊ መካነ መቃብርና ባልቲሙር ፎርት ማካሄነሪ የሚገኘው እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1812 ጦርነት በተካሄደበት ታሪካዊ ቦታ ተገኝተው የአበባ ጉንጉን ለማስቀመጥ ዕቅድ ይዘዋል። ይህን እቅድ የተቃወሙት የባልቲሙር ከንቲባ ጃክ ያንግ ትራምፕ ወደ ባልቲሙር ዝር እንዳይሉ መልዕክት ልከዋል። ድርጊቱ በስቴቱ የተላለፈውን ቤት ውስጥ የመቀመጥ ውሳኔና የጉዞ እቀባን የሚጥስ በመኾኑ ለሰዎች የተሳሳተ መልዕክት ያስተላልፋል ብለዋል። ከንቲባው ጃክ አያይዘውም ፕሬዚዳንት ትራም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ለጉብኝት የያዙት እቅድ አስፈላጊ አይደለም ብለዋል።
በሌላ በኩል የጤና ባለሞያዎችና ባለሥልጣናት ወደ ባህር ዳርቻ ሄደው በመዝናናት ላይ የሚገኙ ሰዎች ቢያንስ አካላዊ መራራቃቸውን እንዲጠብቁና ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እየጎተጎቱ ይገኛሉ።
በዋይት ሃውስ የሚገኘው የኮሮረና ቫይረስ መከላከል ግብረ ሃይል አባል ዶክተር ዴቦራ በርክስ በበኩላቸው ትናንትና እና ከትናንት በስቲያ ሰዎች ወደ ውጭ ወጥው በመዋኛ ቦታዎች እና በመዝናኛ ቦታዎች ላይ ያለ ፊት መሸፈኛ ያደርጓቸው የነበሩ መዝናናቶች በቪዲዮና በፎቶ ታይተዋል። ይህ ደግሞ ሁኔታውን በጣም አሳሳቢ ያደርገዋል ብለዋል።
“ውጭ መሆን እንደሚረዳ እናውቃለን። ፀሐይም ቫይረሱን ለመግደል አስተዋፆ እንዳለው እናውቃለን ነገር ግን ይህ ሁኔታ ሰዎች ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ርቀታቸውን ጠብቀው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ግዴታ የመሆኑን እውነት አይቀይረውም ብለዋል” ዴቦራ ትናንት እሁድ ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ ምልልስ።
በመላው የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ አሜሪካውያን ቫይረሱ፣ በእርግጥም ውጭ ላይ መኖሩን በተመለከት ግልፅ መልዕክት ተላፎላቸዋል ገብቷቸዋልም የሚል ተስፋ ነበረኝ ብለዋል። ባዩት ነገር ማዘናቸውን የገለፁት ዶ/ር ዴቦራ።
ከዩናይትድ ስቴትስ በኮሮና ቫይረስ ክፉኛ የተጠቃችው ኒዩርክ ገዢ አንድሪው ኩሞ፤ “ግዛቱን እንደገና የመክፈት ምዕራፍ ላይ እንገኛለን” ብለዋል። አሁን እየተያ ባለው የቁጥር መረጃ ኒዩርክን ወደ መከፈቱ አቅጣጫ እየወሰዳት ነው ብለዋል። ፈረንሳይ ለስደተኛ ሠራተኞችና ከአውሮፓ አገሪቱን ለመጎብኘት ለሚፈልጉ ጎብኚዎች ድንበሯን ከዛሬ ጀምሮ ክፍት አድርጋለች።
ስፔንም የተወሰኑ የባህር ዳርቻዎችን ክፍት አድርጋለች። ማድሪድና ባርሴሎናም ከ10 ሰዎች በላይ የሚታደሙበትና በቡድን የሚደረጉ እንደ ሙዚየም መጎብኘት እና ውጪ ላይ ባሉ ሬስቶራንቶች የሚደረጉ መዝናናቶችን በግማሽ እንዲካሄዱ ፈቅዳለች። ብራዚል ሌላ መልክ ይዛለች። ዛሬ 653 ሰዎች በብራዚል ሕይወታቸውን አጥተዋል። 360 ሺሕ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ በመያዛቸው ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥሎ ሁለተኛ ሃገር ሆናለች።
የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በመንግሥታቸው የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ባነሱበት ወቅት በአገሪቱ የሚገኘው የቤዝ- ቦል ተጫዋቾ ቡድን ደጋፊዎቻቸው በሌሉበት በመጪው ሰኔ 19 ውድድር የመጀመር እቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል።
ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ ከነገ ማክሰኞ ጀምሮ በታክሲና በሕዝብ ትራንስፖርት የሚገለገል ማንኛውም ሰው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ እንዲያደርግ ግዴታ አስቀምጣለች። ከዕረቡ ጀምሮ ደግም ለየትኛውም የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር በረራ ማስክ ማድረግ የ “ውዴታ” ሳይሆን የ “ግዴታ” እንዲሆን መመሪያ ተቀምጧል።
ኮሮና ቫይረስ ዓለም እያስጨነቀ ባለበት በዚህ ወቅት ዛሬ ሰኞ የሚከበረው ሚሞሪያል ዴይ የአውሮፓዊያኑ ግንቦት ወር በገባ በመጨረሻው ሰኞ ብሔራዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር የተደነገገው በ1971 ዓ.ም ነው። በ245 የአሜሪካን ዕድሜ ውስጥ 1.1 ሚሊዮን የሚገመቱ አሜሪካዊያ በጦርነቶች እና በእርስ በእርስ ግጭቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ዛሬ ደግሞ በኮሮናቫይረስ ምክኒያት የ100 ሺሕ ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል።