የባይደን አስተዳደር የኮቪድ-19 ቫይረስ በረጅም ጊዜ የሚያስክትለውን የጤንነት ቀውስ ለመካለከል አዲስ ብሄራዊ እቅድ እንዲወጣ ትናንት ማክሰኞ አዲስ ትዕዛዝ አውጥቷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የድካም ምልክት፣ ጭንቅላትን የሚዳርግ ጭጋግ፣ ህመምና የትንፋሽ ማጠርን የመሳሰሉ የጤና እክሎችን የሚያካትት መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በዩናይትድ ስቴትስ የጤናና የሰብአዊ አገልግሎት ሚኒስቴር በአዲሱ እቅድ መሰረት የጤና እንክብካቤና የአካል ጉዳት አገልግሎት በኮቪድ-19 ለተጠቁ ሰዎች እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡
የጤናና ሰብአዊ አገልግሎት ሚኒስትር ዝቪየር ቢሴራ እንዲህ ብለዋል፤
“ፕሬዚዳንቱ በሰጡት መመሪያ የጤናና ሰብአዊ አገግሎት በመንግሥት የሚካሄደውን መጠነ ሰፊ የኮቪድ-19 ምላሽ ይመራል፡፡ በዚህም በሦስት ዋና ዋና ግቦች ያተኩራል፡፡ እንክብካቤን ማሻሻል፣ ኮቪድ የረጅም ጊዜ እክል ለፈጠረባቸው ሰዎች የሚሰጥ አገልግሎት፣ ትምህርትና ተደራሽነትን በግሉ ዘርፍና በህክምናው ማኅበረሰብ ማስፋት፣ እንዲሁም ሁለቱንም ግቦች ለማሳካት ምርምሮችን ማካሄድ ናቸው፡፡
በርግጥ ይህን ስናደርግ ኮቪድ-19ን የበለጠ ለመረዳት ከአካዳሚው፣ ከኢንደስትሪው፣ በክፍለ ግዛትና በፌዴራል ደረጃ ካሉ አጋሮቻችን ጋር እንሰራለን፡፡
በእነዚህ ሁሉ ነገሮች ኮቪድ-19 በረጅም ጊዜ ውስጥ በጣም የሚጎዳው የትኛው የህብረተሰባችንን ክፍል እንደሆነ በማየት አስፈላጊውን እርዳታ ማግኘታቸውን እናረጋግጣለን፡፡”
ዋይት ኃውስ የጤናና ሰብአዊ አገግሎትን ለመርዳት ጥናቱ በብሄራዊ የጤና ተቋም ምርምር የሚታገዝበትና በሁሉም የመንግሥት ተቋማት ተግባራዊ የሚደረግበት መንገድ እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ዋይት ኃውስ ለረጅም ጊዜ የጤንነት እክል የሚያስከትል የኮቪድ-19 ተጋላጫነት እንደ አካል ጉዳተኝነት የሚታይ መሆኑን አስታውቋል፡፡