የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ለይፋዊ ጉብኝት ዋሽንግተን የሚገኙትን የጃፓኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳን በዋይት ኃውስ ተቀብለዋቸዋል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመው ጉብኝት፣ ቻይና በፓሲፊክ ቀጠና የበላይነቷን ለማሳየት የምታደርገውን ጥረት ለመግታት ያለመ ነው ተብሏል።
ባይደን እና ኪሺዳ፣ በጃፓን የሚገኘውንና፣ 54ሺሕ ወታደሮች የሚገኙበት የአሜሪካ የጦር ዕዝ የሚጠናከርበትን ዕቅድ ይፋ ያደርጋሉ ተብሏል። በዝግ ውይይት ካደረጉ በኋላም ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡም ይጠበቃል።
በተጨማሪም ጃፓን በአሜሪካ የሕዋ ምርምር ተቋም (ናሳ) ሥር በሚካሄደው የጨረቃ ፕሮግራም ተሳታፊ እንደምትሆን ይፋ ያደርጋሉ ተብሏል።
ፒትስበርግ የሚገኝ አንድ የአሜሪካ የብረት ማምረቻን፣ ለጃፓን የብረት አምራች ኩባንያ በ14.1 ቢሊዮን ዶላር ለመሸጥ ስምምነት ላይ መደረሱ ግን፣ ዲፕሎማሲያዊ ሥነ ስርዓቱ ላይ ጥላ አጥልቷል ተብሏል።
ባይደን ባለፈው ወር በስምምነቱ ላይ ተቃውሟቸውን ሲገልጹ፣ ተቀናቃኛቸው ዶናልድ ትረምፕ ደግሞ በፕሬዝደንትነት የሚመረጡ ከሆነ ስምምነቱን እንደሚያስቆሙ ዝተዋል።
የፊሊፒንሱ መሪ ፈርዲናንድ ማርቆስ (ሁለተኛ) ሁለቱን መሪዎች የሚቀላቀሏቸው ሲሆን፣ ከነገ ሐሙስ ጀምሮ የሶስትዮሽ ጉባዔ እንደሚያካሂዱ ይጠበቃል።
መድረክ / ፎረም