የኮሮናቫይረስ ስርጭቱ እየተባባሰ በመምጣቱ ዩናይትድ ስቴትስ ዜጎቿን ከሁለት ወር በኋላ የቶኪዮ ኦሊምፒክስን ወደምታስተናግደው ወደጃፓን እንዳይጓዙ አስጠነቀቀች።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጃፓን የምታካሂደው የፀረ ኮቪድ-19 ክትባት እንቅስቃሴ ዝግተኛ መሆኑን እና ጃፓን ራሷም ከዩናይትድ ስቴትስ በሚጓዙ መንገደኞች ላይ ገደብ መጣሏን ምክንያት በማድረግ ለአሜሪካውያን ከፍተኛውን የጉዞ ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።
የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል /ሲዲሲ/ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ የኮቪድ-19ኝ ክትባታቸውን ወስደው ያጠናቀቁም ዜጎች ቢሆኑ ለተለያዩ የኮሮናቫይረስ ዝርያዎች የመጋለጥ እና ወደሌሎች የማዛመት አደጋ ሊገጥማቸው ስለሚችል በጠቅላላው ወደጃፓን ከመጓዝ ሊቆጠቡ ይገባል ሲል አስጠንቅቋል።
ባለፈው ዓመት ኮቪድ-19 በዓለም ዙሪያ መዛመቱን ተከትሎ እንዲዘገይ የተደረገው የቶኪዮ ኦሊምፒክስ ውድድር እአአ ከሃምሌ 23 እስከ ነሃሴ 8 ይካሄዳል።
ይሁን እንጂ በዋና ከተማዋ ቶኪዮ እና ሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች እየጨመረ የመጣውን የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር አስቸኳይ ጊዜ ታውጇል። የሀገሪቱ ሆስፒታሎች በህሙማን ብዛት እየተጨናነቁ ሲሆን የኦሊምፕክስ ውድድሮቹ እንዲሰረዙ ከህዝቡ የሚቀርበው ውትወታ እየጨመረ መጥቷል።
በቅርቡም 6000 ሃኪሞች እና የሆስፒታል ሰራተኞች የሚወክል የጃፓን የህክምና ባለሙያዎች ማኅበር በፃፈው ግልጽ ደብዳቤ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዮሺሂዴ ሱጋ ውድድሩ መሰረዝ እንዳለበት ዓለም አቀፍ የኦሊምፒክ ኮሚቴን እንዲያሳምኑ ጠይቋል።
በቫይረሱ ስርጭት መባባስ የተነሳ ቀደም ብለው የጃፓን ባለሥልጣናት የውጭ ሃገር ሰዎች በውድድሩ ላይ ለመገኘት እንዳይገቡ ከልክለዋል። ሆኖም የሀገሪቱ ካቢኔ ዋና ጸኃፊ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል ክልከላው የግድ አስፈላጊ በሆነ ምክንያት የሚመጡትን አይመለከትም ብለዋል። በማስከተልም ዩናይትድ ስቴትስ ውድድሩ እንዲካሄድ ያላትን ድጋፍ በተመለከተ ያስተዋልነው የተለወጠ ነገር የለም ብለዋል።
በዩናይትድ ስቴትሱ የጃንስ ሃፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የኮቪድ-19 መረጃ ማዕከል መሰረት እስካሁን ጃፓን ውስጥ የተመዘገቡት የተረጋገጡ የኮሮናቫይረስ ተጋላጮች 722 668 ሲሆኑ 12351 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። በጠቅላላው የኮቪድ መከላከያ ክትባቱን የተከተቡት ደግሞ ከህዝቡ አምስት ከመቶው ብቻ መሆናቸውን መረጃው ያመለክታል።