የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን ዛሬ ማክሰኞ በዋይት ሀውስ ተቀብለው ያነጋግራሉ።
የሁለቱ መሪዎች ንግግር የመጣው ጋዛ ውስጥ የቀሩት ታጋቾች በሙሉ መለቀቅን፣ የውጊያው ሙሉ በሙሉ በቋሚነት መቆምን እና የእስራኤልን ኃይሎች ከጋዛ ተጠቃሎ መውጣት ጨምሮ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ከወሳኝ ምዕራፍ በደረሰበት ወቅት ነው። እስራኤል እና ሃማስ በደረሱት ስምምነት መሰረት የውላቸውን ሁለተኛው ዙር አፈጻጸም ተግባራዊ ለማድረግ ከአራት ሳምንታት ያነሰ ጊዜ ነው የቀረው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ “ሰላሙ ስለመያዙ የምሰጠው ዋስትና የለም” ሲሉ ትረምፕ ትላንት ሰኞ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ኔታንያሁ በዋይት ሃውስ ከፕሬዝዳንት ትረምፕ ጋር ከሚያደረጉት ውይይት አስቀድሞ የጋዛውን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማሳካት ግፊት ሲያደርጉ ከነበሩት ውስጥ አንዱ ከሆኑት ከዩናይትድ ስቴትሱ የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ጋር ትላንት ሰኞ ተገናኝተው ተነጋግረዋል።
ውይይቱን ተከትሎም የኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፡ “ስብሰባው አዎንታዊ እና ወዳጅነት የተመላ ነበር” ብሏል። ኔታንያሁ ወደ ሃገራቸው ሲመለሱም የስምምነቱን ሁለተኛ ምዕራፍ በሚመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ በእስራኤል አጠቃላይ አቋም ላይ ለመወያየት ከደኅንነት ካቢኔያቸው ጋር እንደሚወያዩ ጠቁሟል።
ዊትኮፍ በበኩላቸው ስምምነቱን ለማሳካት ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በመተባበር ከሰሩት ኳታር እና ግብፅ ባለስልጣናት ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
መድረክ / ፎረም