የፊታችን ረቡዕ ጥር 12 የሚከናወነው የጆ ባይደን የቃለመሃላና የሲመት ሥርዓት እጅግ በተጠናከረው የፀጥታ ጥበቃ ምክንያት ከወትሮው የተቀዛቀዘ እንደሚሆን ተገልጿል።
ባላፈው ሣምንት ውስጥ ሁከተኞች በተወካዮች ምክር ቤቱ ላይ ካደረሱት የህይወት ያጠፋ ጥቃት በኋላ ወትሮ ከተወካዮች ምክር ቤቱ ህንፃ ፊት ለፊት የተዘረጋውን ግዙፍ አደባባይ ይሞሉ የነበሩ ታዳሚዎችና የበዓሉ አክባሪዎች በዚህ ዓመት የማይገኙ ከመሆኑም በላይ የምክር ቤቱ አካባቢና ዋና ከተማይቱ ዋሺንግተን ዲሲ በ21 ሺህ ወታደሮች እንደሚጠበቁ ተገልጿል።
ይህ የወታደሮች ቁጥር ዩናይትድ ስቴትስ ኢራቅ፣ አፍጋኒስታንና ሦሪያ ውስጥ ካዘመታቸው ተዋጊዎቿ ቁጥር የሚበልጥ እንደሆነም ተናግሯል።
የዛሬ አራት ዓመት የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ቃለመሃላ ሥርዓት ሲከናወን ለጥበቃ የተሠማራው ወታደር 8 ሺህ ነበር።
ጥበቃ ላይ የተሠማሩትን ወታደሮች ትናንት ድንገት ተገኝተው የተመለከቱት ም/ፕ ማይክ ፔንስ የሽግግሩ ሥር ዓት እንደሚፈፀምና ደህንነቱ የተጠበቀ በዓለ ሲመት እንዲሆን ለማድረግ የትረምፕ አስተዳደር በቁጥር አቋም እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ዋሺንግተን ዲሲ ላይና በሃምሳዎቹም ግዛቶቹ ዋና ከተሞች ውስጥ በትጥቅ የታገዘ ጥቃት ለመሠንዘር ዛቻዎች ቢሰሙም ህግ አስከባሪዎች ባለሥልጣናት ግን ሥነ ሥርዓቱ በሰላማዊ ሁኔታ እንደሚፈፀም ያላቸውን መተማመን እየገለጹ ነው።