ዋሽንግተን በቴህራን እና በኢራን በሚደገፉ ቡድኖች ላይ ዛሬ ሀሙስ ተጨማሪ ማዕቀቦች መጣሏን የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሁቲና ሂዝቦላን የንግድ መረቦችን ኢላማ ያደረገው ማዕቀብ የተጣለው ዩናይትድ ስቴትስ በቴህራን እና በኢራን በሚደገፉ ቡድኖች ላይ ያሳደረችውን ጫና ከፍ ባደረገችበት ወቅት ነው፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ ገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ማዕቀቡ ለሁቲ የፋይናንስ ባለሥልጣናት፣ ዘይትና ፈሳሽ ጋዝን ጨምሮ የኢራን ሽቀጦችን ወደ የመን እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በማጓጓዝ ተሳትፈዋል በሚል የተከሰሱትን ኢላማ ያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የሚኒስቴሩ መግለጫ በሰኢድ አል-ጀማል ከተዘረጋው መረብ የሚገኘው ገቢ በቀይ ባህር ላይ የተሰማሩትን እቃ አጓጓዥ መርከቦችና የሲቪሎችን መሰረተ ልማት ኢላማ ያደረጉትን የሁቲዎች ጥቃት ይደግፋል ብለዋል፡፡
በቀይ ባህር ላይ በተሰማሩ የንግድ መርከቦች ላይ በኢራን በሚደገፉ የሁቲ ሚሊሻዎች የሚደርሰው ጥቃት የምስራቅ-ምዕራብ የንግድ መስመሮችን እያስተጓጎለ ነው፡፡
የማጓጓዣ ወጪዎችንም በመጨመር በእስያና በአውሮፓ ወደቦች መጨናነቅ እንዲፈጠር እያደረገ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በዛሬው ሀሙስ የማዕቀቡ ኢላማ የተደረገው መሰረቱን በሆንግ ኮንግ ያደረገውን የመርከብ ሥራ አስኪያጅ ሠራተኞችና በርካታ የነዳጅ ማጓጓዣ ማጠራቀሚያዎችን ጨምሮ የሂዝቦላው የፈሳሽ ነዳጅ ዘይት ማጓጓዣ መሆኑንም የሚኒስቴሩ መግለጫ አክሎ ገልጿል፡፡
በሂዝቦላ ቁጥጥር ስር ያለው የታላቂ ቡድን ሁለት የነዳጅ ማመላለሻዎችን በመጠቀም አስር ሚሊዮን ዶላሮች የሚያወጡ የነዳጅ ፍሳሽ ዘይቶችን ከኢራን ወደ ቻይና እንደሚያስተላለፍ የአሜሪካው ገንዘብ ሚኒስቴር መግለጫ አመልከቷል፡፡
በሚኒስቴሩ የሽብርተኝነት እና የፋይናንሺያል ኢንተለጀንስ ተጠባባቂ ምክትል ኃልፊ ብራድሌይ ስሚዝ “የዛሬው እርምጃ ፣ ኢራን በክልሉ አሸባሪዎች ለሆኑት እንደ ሊባኖሱ ሂዝቦላህና ሁቲ ላሉ ወኪሎችዋ የምትልከውን ዋነኛ የገንዘብ ምንጭ ለመዝጋት ያለንን ቁርጠኝነት አጉልቶ ያሳያል” ብለዋል፡፡
ስሚዝ "የእኛ መልእክት ግልጽ ነው የእነዚህን ቡድኖች የማተራመስ ተግባራትን በገንዘብ መደገፍ የሚፈልጉ ሁሉ ተጠያቂ ይሆናሉ።" ሲሉ አክለዋል፡፡
የዛሬው እርምጃ ኢላማ በተደረገባቸው ተቋማት ያሉትን ማናቸውንም የዩናይትድ ስቴትስ ይዞታዎች የሚያግድ ሲሆን ከተቋማቱም ጋር አሜሪካውያን ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖራቸው ይከለክላል፡፡”
የፋይናንስ ተቋማት እና ጋር አንዳንድ የገንዘብ ልልውጦችን የሚያደርጉም ሌሎች ቢኖሩ ማዕቀቡ እንደሚመለከታቸው ተገልጿል፡፡
መድረክ / ፎረም