ሁቲዎች ከሚቆጣጠሩት የየመን አካባቢ ኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ በቆመ የንግድ መርከብ ላይ ትናንት ረቡዕ በተተኮሰ ሚሳይል ሦስት የመርከቡ ሠራተኞች መገደላቸውን የዩናይትድ ስቴትስ ማዕከላዊ እዝ አስታወቀ፡፡
በኢራን የሚደገፉት ሁቲ ታጣቂዎች በዓለም አቀፉ የንግድ መርከቦች መተላለፊያ መስመር ላይ እአአ ባለፈው ህዳር አጋማሽ በተከታታይ ጥቃት ማድረስ ከጀመረ ወዲህ በጥቃቱ የሰው ህይወት ሲጠፋ የትናንቱ የመጀመሪያ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የዩናይትድ ስቴትሱ የጦር ኃይል ማዕከላዊ እዝ ሴንትኮም እንዳስታወቀው ሁቲዎቹ ታጣቂዎች በሁለት ቀን ውስጥ አምስት ሚሳይል ተኩሰዋል፡፡
ትናንት ሁቲዎቹ የተኮሱት ሚሳይል የመታው በባርቤዶስ ስም የተመዘገበ ንብረትነቱ የላይቤሪያ የንግድ መርከብ ሲሆን በመርከቡ ጉዞ መቆጣጠሪያ ክፍል ላይ ቃጠሎ ማስነሳቱን የመከላከያ ባለስልጣናት ለቪኦኤ አመልክተዋል፡፡ በጥቃቱ አራት የመርከቡ ሠራተኞች የቆሰሉ ሲሆን ሦስቱ በአእስጊ ሁኔታ መጎዳታቸውን ገልጸዋል፡፡ ፊሊፒንስ ከተገደሉት የመርከቡ ሠራተኞች መካከል ሁለቱ ከቆሰሉትም መካከል ሁለቱ ዜጎቿ መሆናቸውን አስታውቃለች፡፡
ዩኤስኤስ ፊሊፒን ሲ (USS PHILIPINE SEA) የተባለ ሚሳይል ተሸካሚ መርከብ መርከበኞቹን ለመርዳት ተንቀሳቅሶ እንደነበር አንድ የእዙ ባለስልጣን ገልጸው እርዳታ ለመስጠት መጀመሪያ የደረሰው የህንድ አውዳሚ መርከብ መሆኑን አክለው ጠቅሰዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች ትናንት በሰጡት ቃል “በሁቲዎቹ ታጣቂዎች ጥቃት በሰው ሕይወት፡ በንብረት እና በተፈጥሮ አካባቢ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት እያየን ነው፡፡ ሁቲዎቹ በቀይ ባሕር በዓለም አቀፍ የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያቆሙ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል፡፡
መድረክ / ፎረም