ለዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔነት በሦስት ቀናት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ የተወዳደሩት የኦሃዮው ሪፐብሊካን እንደራሴ ጂም ጆርዳን ዛሬም ለመዶሻው የሚያበቃቸውን ድምፅ ሳያገኙ ቀርተዋል።
ዛሬ፤ ዓርብ የምክር ቤቱ ሙሉ ጉባዔ ባካሄደው ግልፅ ድምፅ አሰጣጥ የራሳቸው ፓርቲ አባላት የሆኑ ሃያ አምስት እንደራሴዎች ሳይደግፏቸው ቀርተዋል።
በምክር ቤቱ የዛሬ ጉባዔ ላይ የተገኙት ህዳጣኑ ዴሞክራቲክ ህግ አውጭዎች ከመሪያቸው የኒው ዮርኩ እንደራሴ ሃኪም ጄፍሪስ ጀርባ በፅናት ቆመዋል።
435 መቀመጫ ላለው የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስ አፈጉባዔ ለመሆን ቢያንስ የ217 እንደራሴዎችን ድምፅ ማግኘት የሚገባ ሲሆን በዛሬው ሥነ ሥርዓት ማንኛውም ተፎካካሪ እዚያ መድረስ አልቻለም።
ጆርዳን ባሳለፏቸው ሦስት ዙሮች የሚቃወሟቸው ሪፐብሊካን ቁጥር እያደገ መጥቶ ከመጀመሪያው 18 ዛሬ 23 ደርሷል።
የቀድሞው አፈጉባዔ የካሊፎርኒያው እንደራሴ ኬቭን ማካርቲ በስምንት ሪፐብሊካንና በሙሉ ዴሞክራቶች ድምፅ ከመንበሩ ከተወገዱ ወዲህ ኮንግረሱ ለሁለት ሣምንታት ያለመሪና ተሽመድምዶ የሚገኝ ሲሆን አዲስ መሪ እስኪኖረው በአንድም የወጭ ህግ ላይ ድምፅ መስጠት አይችልም።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እሥራዔል ሃማስ ላይ፤ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር እያካሄዱ ላሏቸው ጦርነቶች መደገፊያ የሚውል የ106 ቢሊየን ዶላር ጥያቄ ዛሬ ለመላክ ተዘጋጅተዋል።
መድረክ / ፎረም