የሀገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ‘ተጓተተ’ ባለው ስደተኞችን ከሀገር የማስወጣት ሥራ የተነሳ፣ የኢሚግሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኃላፊውን በዐዲስ አመራር ተካ።
የሀገር ውስጥ ደኅንነት ሚንስትሯ ክሪስቲ ኖም በትላንትናው ዕለት የኢሚግሬሽን እና የጉምሩክ ጉዳዮች አስፈጻሚ መሥሪያ ቤት አስተዳዳሪን ከሥራ ኃላፊነታቸው በማንሳት በዐዲስ ተክተዋል።
ለዚህም ምክኒያቱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ‘አሳካለሁ’ ያሉትን እና “በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የፈለሱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ስደተኞች ከሀገር ለማስወጣት የተያዘ ዕቅድ ዕውን ለማድረግ ነው” ተብሏል።
ትራምፕ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን ከሀገር ለማባረር የገቡት ቃል የምርጫ ዘመቻቸው አብይ ትኩረት አድርገውት እንደነበር ይታወሳል። የዩናይትድ ስቴትስ የኢሚግሬሽን እና የጉምሩክ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤት ተጠባባቂ ድሬክተር ካሌብ ቪቴሎ፣ አስተዳደሩ በአጭር ጊዜ እውን ለማድረግ ያቀደውን ‘ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌለው ስደተኛ ከሀገር የማስወጣት ጥረት አላሳኩም’ በሚል ወደ ሌላ የሥራ መደብ እንዲዛወሩ መደረጋቸውን ሮይተርስ ቀደም ሲል ዘግቧል።
ሮይተርስ የዩናይትድ ስቴትስ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚንስቴርን መረጃ ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው፤ የትራምፕ አስተዳደር በሥልጣን ዘመኑ የመጀመሪያ ወር ቁጥራቸው 37 ሺሕ 660 የሚደርሱ ስደተኞችን ሀገር አስወጥቷል። ይሁንና አሃዙ 57 ሺሕ ከሚደርሰው የጆ ባይደን አስተዳደር በሥልጣን ዘመኑ የመጨረሻው ዓመት በየወሩ ከሀገር ካስወጣቸው ስደተኞች በአማካይ ቁጥር በእጅጉ ያነሰ መሆኑ ተመልክቷል።
ሚንስትር ኖም ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፤ የድርጅቱ ተጠባባቂ ድሬክተር የነበሩትን ቶድ ሊዮንን ተጠባባቂ ድሬክተር፣ የሉዊዚያና ክፍለ ግዛቱን የዱር እንስሳትና ዓሳ ሀብት መምሪያ ኃላፊ ደግሞ የድርጅቱ ምክትል ድሬክተር አድርገው መሾማቸውን ይፋ አድርገዋል።
"ፕሬዚዳንት ትራምፕ እና የአሜሪካ ሕዝብ በመሰረቱ የሚጠብቁብንን ተገቢ ውጤት እውን ለማድረግ የኢሚግሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ባለሥልጣኑን የሚመሩ ዐዲስ አመራሮች ሰይሜያለሁ" ሲሉ ያስታወቁት ኖም፣ “ሊዮን እና ሺሃን የአሜሪካ ህዝብ ሕገ-ወጥ የውጭ ዜጎችን ባሉበት ለመያዝ እና ከሃገር ለማባረር የአሜሪካ ሕዝብ የሰጠንን ኃላፊነት ለሥኬት ለማብቃት በተያዘ ውጥን "የኢሚግሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ባለሥልጣንን ሠራተኞ ይመራሉ " ሲሉ በመግለጫቸው አክለው አስታውቀዋል።
መድረክ / ፎረም