ዩናይትድ ስቴትስ ከአንድ መቶ ለሚበልጡ የዓለም ሀገሮች የለገሰችው የኮቪድ-19 ክትባት ድጋፍ በዛሬው ዕለት ሁለት መቶ ሚሊዮን ደፍኗል።
ይህንኑ አስመልክቶም ኋይት ሀውስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን "ለዓለም የክትባቱን ክምችት መገኛ እንሆናለን" ሲሉ የገቡትን ቃል ያሳካ ብሎታል።
የዩናይትድ ስቴትስ የዓለም አቀፍ ልማት ተራድዖ ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር በሰጡት ቃል "ዛሬ አሜሪካውያንን የሚያኮራን ሁለት መቶ ሚሊዮን ምክንያት አግኝተናል" ብለው ዩኤስኤድ ይህን በዓለም ላይ ታይቶ በማያውቅ ደረጃ የከበደ ወረርሽኝ ለመዋጋት እየተደረገ ባለው ከምንጊዜውም የገዘፈ እና የተፋጠነ እንዲሁም የተወሳሰበ የክትባት ዘመቻ በግንባር ቀደምነት በመሰለፉ ኩራት ይሰማናል ብለዋል።
የኮቪድ-19 ክትባት ድጋፉ በተፋጠነ መንገድ ለባለዝቅተኛ ገቢ ሀገሮች ተልኳል። ባለፈው ሳምንትም ኋይት ሀውስ በሰጠው መግለጫ ለአፍሪካ ህብረት አስራ ሰባት ሚሊዮን የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባቶች እንደሚልክ አስታውቋል። ይህም ሃምሳ አምስት አባል ሀገሮች ላሉት ድርጅት ዩናይትድ ስቴትስ የላከችውን የክትባት ድጋፍ ወደሃምሳ አምስት ሚሊዮን ነጠላ ክትባቶች ያሳድገዋል።
ባለፈው መስከረም ወር ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ዩናይትድ ስቴትስ ለባለዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ሃገሮች ከአንድ ቢሊዮን በላይ ክትባቶች ለመለገስ ዕቅድ እንዳላት ይፋ ማደረጋቸው ይታወሳል።
ዩኤስኤድ ለሀገሮቹ ተያያዥ መመርመሪያዎቹን፥ መድሃኒቶችን እና ቫይረሱን መከላከያ መሳሪያዎች ጨምሮ ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጧል።
በሌላ በኩል ኋይት ሀውስ በዓለም ዙሪያ ክትባቱ ለብዙዎች ባልተዳረሰበት በዚህ ወቅት የኮቪድ-19 ክትባት የወሰዱ አሜሪካውያን ማጠናከሪያ ክትባት እንዲወስዱ ግፊት እያደረገ ነው የሚል ነቀፋ ገጥሞታል። የአስተዳደሩ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ነቀፌታው ተገቢ እንዳልሆነ ይናገራሉ። አሜሪካውያንን ከቫይረሱ እየጠበቅን ክትባቱን ለሌሎችም ማካፈል እንችላለን ብለዋል።