በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሐማስ የትረምፕ አስተያየት እስራኤል ከስምምነቱ እንድታፈገፍግ ያበረታታል አለ


በሰሜናዊ ጋዛ ሰርጥ በእስራኤል የቦምብ ጥቃት የወደሙ ሕንፃዎች ምስል፣ የካቲት 25 ቀን 2017 ዓ.ም.
በሰሜናዊ ጋዛ ሰርጥ በእስራኤል የቦምብ ጥቃት የወደሙ ሕንፃዎች ምስል፣ የካቲት 25 ቀን 2017 ዓ.ም.

ዩናይትድ ስቴትስ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሐማስ “የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ ዛቻዎች እስራኤል ከጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንድትወጣ እያበረታታ ነው” ሲል ዛሬ ሐሙስ ተናገረ።

ሐማስ ይህን የገለጸው፣ ትረምፕ ሐማስ ጋዛ የሚገኙ ቀሪዎቹን ታጋቾች ካልፈታ “ ከባድ ቅጣት ያገኘዋል” ካሉ አንድ ቀን በኋላ ነው።

ትረምፕ ትሩዝ ሶሻል በተባለው የማኅበራዊ መገናኛ መድረካቸው ላይ “ሁሉንም ታጋቾች ሳይዘገይ፣ አሁኑኑ ልቀቁ ፣ የገደላችኋቸውን ሰዎች አስከሬንም በሙሉ አሁኑኑ መልሱ፡፡ ካልሆነ አለቀላችሁ።” ብለዋል፡፡

ትረምፕ አክለውም “እስራኤል ሥራውን ለማጠናቀቅ የሚያስፈልጋትን ሁሉን ነገር እየላኩ ነው፡፡ ያልኩትን ካላደረጋችሁ አንድም የሐማስ አባል አይተርፍም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

የተኩስ አቁሙ የመጀመሪያው ምዕራፍ ባለፈው ቅዳሜ አብቅቷል። በስምምነቱ መሠረት ሐማስ 33 እስራኤላውያን ታጋቾችን እና አምስት የታይላንድ ዜጎችን ሲለቅ፣ እስራኤል 2 ሺሕ የሚጠጉ የፍልስጤም እስረኞች ለቃለች።

ኋይት ሀውስ ከሐማስ ጋራ በቀጥታ ውይይት ማድረጉን ትላንት ረቡዕ አረጋግጧል። “ውይይቱ ያተኮረው አሁንም በጋዛ ታግተው የሚገኙ አሜሪካውያንን ስለ መልቀቅ ነው” ሲሉ፣ ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ምንጮች ገልጸዋል።

የኋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ካሮላይን ሌቪት ንግግሮቹን “ለአሜሪካ ሕዝብ የሚጠቅመውን ለማድረግ በቅን ልቦና የተደረገ ጥረት ነው” ሲሉ ገልፀውታል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት በሰጠው መግለጫ ደግሞ እስራኤል "ከሐማስ ጋራ በቀጥታ መነጋገርን በሚመለከት ያላትን አቋም ለአሜሪካ አስታውቃለች" ብሏል።

የጋዛ ጦርነት የጀመረው፣ ሐማስ እ.ኤ.አ ጥቅምት 2023 እስራኤል ላይ ባደረሰው ድንገተኛ ጥቃት፣ 1ሺሕ 200 የሚጠጉ ሰዎችን ከገደለ እና 250 ሰዎች አግቶ ከወሰደ በኋላ ነበር።

እስራኤል በአፀፋው ጋዛ ላይ በወሰደችው ጥቃት ከ48 ሺሕ 400 በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ሲል የጋዛው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG