በመጠናቀቅ ላይ ባለው የፈረንጆች ዓመት አሜሪካ 14.2 ቢሊዮን ዶላር ግምት ያላቸው በመቶ የሚቆጠሩ የንግድ እና የመዋዕለ ነዋይ ስምምነቶችን ከአፍሪካ ጋራ እንደፈጸመች ባለሥልጣናት ዛሬ አስታውቀዋል። ቻይና በአህጉሪቱ ላይ ያላትን እያደገ የመጣ ተጽእኖ ለመገዳደር ነው ተብሏል።
በዚህ ዓመት የተፈጸሙት 547 የንግድ እና የመዋዕለ ነዋይ ስምምነቶች፣ ከቀደመው ዓመት ሲነጻጸር በቁጥርም ሆነ በእሴት 67 በመቶ ጭማሪ ያሳዩ መሆኑን “አፍሪካን እናበልጽግ” የተሰኘው የአሜሪካ ተነሳሽነት አስተባባሪ ብሪቲሽ ሮቢንሰን ተናግረዋል።
“የአሜሪካ እና የአፍሪካ ግንኙነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ዓመት ነው” ሲሉ የፕሬዝደንት ባይደን የአፍሪካ ዋና አማካሪ ጀድ ዴቨርመንት በበኩላቸው ተናግረዋል።
አሜሪካ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር ጉባኤ ያደረገችበትን አንደኛ ዓመት በማስመልከት በርቀት በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተናገሩት ሁለቱ ባለስልጣናት፣ ባለፈው ታህሳስ ቃል ከተገባው 55 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ስምምነት፣ አሜሪካ 40 በመቶውን ተግባራዊ እንዳደረገች አስታውቀዋል።
ቻይና በመሠረተ ልማት፣ መዋዕለ ነዋይ እና ብድር በአፍሪካ ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ ላይ በመሆኗ፣ አሜሪካም በህጉሪቱ በንግድ እና መዋዕለ ነዋይ ዘርፍ በስፋት ለመሳተፍ እንደምትሻ ያመላከተ ነው ተብሏል።
መድረክ / ፎረም