በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዩናይትድ ስቴትስ የመሳሪያ ጥቃትን የተቃወሙ ሰልፎች ተካሄዱ


በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች፣ በዋሽንግተን ዲሲ ብሄራዊ አዳራሽ፣ ለሁለተኛ ግዜ 'ለህይወታችን እንሰለፍ' በሚል ያደረጉት ሰልፍ
በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች፣ በዋሽንግተን ዲሲ ብሄራዊ አዳራሽ፣ ለሁለተኛ ግዜ 'ለህይወታችን እንሰለፍ' በሚል ያደረጉት ሰልፍ

በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዋሽንግተን ዲሲ፣ ኒው ዮርክ፣ ፓርክላንድ፣ ፍሎሪዳ እና ሌሎች የዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች ባካሄዱት ሰልፍ ባለፉት ወራት በዩቫልዲ፣ ቴክሳስ፣ ቡፋሎ እና ኒው ዮርክ በተከታታይ የተካሄዱ ጅምላ ግድያዎችን ተከትሎ የአሜሪካ ምክር ቤት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።

በዋሽንግተን ዲሲ ብሄራዊ አዳራሽ፣ ለሁለተኛ ግዜ 'ለህይወታችን እንሰለፍ' በሚል ለተሰባሰቡ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ንግግር ያደረጉት የከተማዋ ከንቲባ ሙሪየል ባውዘር "ሲበቃ፣ ይበቃል" ብለዋል።

"አሁን የምናገረው እንደከንቲባ፣ እንደ እናት እና በሚሊየን የሚቆጠሩ አሜሪካውያንን እና ምክር ቤቱ ስራውን እንዲሰራ የሚጠይቁ የአሜሪካ ከንቲባዎችን ወክዬ ነው" ያሉት ከንቲባዋ "የምክር ቤቱ ሥራ የእኛን ደህንነት መጠበቅ ነው። ልጆቻችንን ከመሳሪያ ጥቃት መጠበቅ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

በዋሽንግተን ዲሲው ሰልፍ ላይ ንግግር ያደረጉት ሌሎች ተናጋሪዎችም በተለይ በዩቫልዲ ሮብ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 19 ህፃናት እና ሁለት አስተማሪዎች መገደላቸውን ተከትሎ፣ ህግ አውጪዎች እርምጃ እንዲወስዱ አለበለዛም እራሳቸውን ከሥልጣን እንዲያገሉ ጠይቀዋል።

እአአ በ2018 በፍሎሪዳ ግዛት ፓርክላንድ ከተማ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ 17 ተማሪዎችን እና የትምህርት ቤቱን ሰራተኞች ከገደለ የመሳሪያ ጥቃት የተረፈው ዴቪድ ሆግ በበኩሉ መንግሥታችን 19 ህፃናትን በገዛ ትምህርት ቤታቸው እንዳይገደሉ ማድረግ ካልቻለ፣ ይህን መንግሥት የምንቀይርበት ጊዜ ነው" ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳናት ጆ ባይደንም ተቃዋሚዎቹ ሰልፋቸውን እንዲቀጥሉ በመንገር ምክር ቤቱ የመሳሪያ ጥቃትን በተመለከተ በሚያደርገው ድርድር ዙሪያ ይላቸው ተስፋ የላላ መሆኑን ገልፀዋል።

ባይደን በቅርቡ ለሀገሪቱ ባደረጉት ንግግር የመሳሪያ ጥቃት ለማስቆም የዕድሜ ገደብን ከማስቀመጥ ጀምሮ ሌሎች እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጠይቀው ነበር።

XS
SM
MD
LG