በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ለሁለተኛ ቀን ዝግ ሆኖ ዋለ


ዋይት ሃውስ
ዋይት ሃውስ

ምናልባት መንግሥቱን ነገ፤ ሰኞ ለመክፈት የሚያስችል ስምምነት ላይ ለመድረስ በሚል የሁለቱም ፓርቲዎች እንደራሴዎች ማምሻውን በር ዘግተው ስብሰባ ተቀምጠዋል።

ለመንግሥቱ ወጭዎች የተመደበው በጀት በማለቁና ለተጨማሪ ጊዜ የተጠየቀው ወጭ በተወካዮች ምክር ቤቱ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ስምምነት ላይ ሳይደረስ ቀነ-ገደቡ በማለፉ በዋሺንግተን ሰዓት፣ ዓርብ ለቅዳሜ አጥቢያ እኩለ ሌሊት ላይ የተዘጋው የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ዛሬም ለሁለተኛ ቀን ዝግ ሆኖ ውሏል።

በሪፐብሊካን እና ዴሞክራት እንደራሴዎች ወካከል የተነሣው ውዝግብና ፍጥጫም እስከአሁኑ ሰዓት እልባት ባለማግኘቱ መፍትሄ የማግኘትና የመንግሥቱ መልሶ የመከፈት ጉዳይም አሁንም ጥያቄ ውስጥ እንደሆነ ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት ሕንፃ ጉልላትና ከፊቱ የቆመው የሰላም ሃውልት
የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት ሕንፃ ጉልላትና ከፊቱ የቆመው የሰላም ሃውልት

በሌላ በኩል ግን በሕግ መምሪያውም በሕግ መወሰኛውም ምክር ቤቶች አብዝኀ መቀመጫ ያላቸው ያላቸው ሪፐብሊካን እንደራሴዎች እስከዛሬ ሲሠራበት የቆየውን የፍፁም አብላጫ ድምፅ ውሣኔ አካሄድ ያጥፉ እንደሆነ የሚያመላክት የትዊተር መልዕክት የሁለተኛ ዓመት ሥራቸውን ዛሬ የጀመሩት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ አውጥተዋል።

ምንም እንኳ መቶ መቀመጫዎች ባሉት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ውስጥ ሪፐብሊካኑ እንደራሴዎች 51፣ ዴሞክራቶች 49 መቀመጫዎችን የያዙ ቢሆንም በጀትና ሌሎችም ቁልፍ ናቸው የሚባሉ ጉዳዮችን ለመወሰን የስድሣ ሴናተሮች ድምፅ ያስፈልጋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አብዝኀ መሪ ሪፐብሊካን ሚች ማኮኔል (ግራ) እና የአናሳዎቹ መሪ ዴሞክራት ቸክ ሹመር (ቀኝ)
የዩናይትድ ስቴትስ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አብዝኀ መሪ ሪፐብሊካን ሚች ማኮኔል (ግራ) እና የአናሳዎቹ መሪ ዴሞክራት ቸክ ሹመር (ቀኝ)

ፕሬዚዳንቱ ቀደም ባለ ጊዜም የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ክፍት መቀመጫ ለመሙላት ሲሠራበት የቆየውን ይህንን ሕግ ሪፐብሊካኑ ሴናተሮች “ኒኩሌር አማራጭ” በሚባል የቀላል አብላጫ ድምፅ ማለትም የሃምሣ እና አንድ ድምፅ ውሣኔ እንዲያፀድቁላቸው ጠይቀው ተሣክቶላቸዋል።

ፕሬዚዳንቱና ዴሞክራቶቹ እንደራሴዎች የገቡበት ትንቅንቅ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ያለ ሕጋዊ ፈቃድ ከወላጆቻቸው ጋር በሕፃንነታቸው ለገቡ ‘ድሪመርስ / ሕልመኞች’ የሚል የጥቅል መጠሪያ የተሰጣቸው ሰዎች ዘላቂ መፍትኄ እንዲሰጥ በሚልና ፕሬዚዳንቱ “በዩናይትድ ስቴትስና በሜክሲኮ ወሰን ላይ አቆመዋለሁ” ላሉት ግንብ ገንዘብ እንዲሰጣቸው ባቀረቡት ጥያቄ ዙሪያ የተውተበተበ መሆኑ ታውቋል።

መንግሥቱ ዝግ ሆኖ በሚቆይባቸው ቀናት ከስምንት መቶ ሺህ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች ያለክፍያ ከሥራ ውጭ ሆነው የሚቆዩ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ሊዘጉ የማይችሉት ተቋማት በጣም አነስተኛ ቁጥር ባለው እጅግ አስፈላጊ ናቸው በሚባሉ ሠራተኞች ኃይል እየተንቀሳቀሰ ይቆያል።

የመንግሥቱ መዘጋት ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ አንደኛ የሥልጣን ዓመት ጋር በመግጠሙ ምክንያት ትናንት፣ ቀዳሜ ፍሎሪዳ በሚገኘው የግላቸው መናፈሻ ማር-አ-ላጎ ተዘጋጅቶ በነበረው የፌሽታና የፈንጠዝያ ዝግጅት ላይ ለመገኘት የነበራቸውን ዕቅድ ሠርዘው ጊዜያቸውን ዋይት ሃውስ ውስጥ ከእንደራሴዎቹ ጋር በመወያየትና በመደራደር አሳልፈዋል።

መንግሥቱ ዝግ ሆኖ በሚዘልቅባቸው ቀናት ከስምንት መቶ ሺህ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች ያለክፍያ ከሥራ ውጭ ሆነው ይቆያሉ።

በማር-አ-ላጎው ዝግጅት ላይ የተገኙት የ150 ሺህ እና የ250 ሺህ ዶላር ቲኬቶችን የገዙ የትረምፕ ደጋፊዎች ሲሆኑ ከሦስት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለሚካሄደው መጭው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚስተር ትረምፕ ሁለተኛ ዙር ሥልጣን ዘመቻ ኮሚቴ የገብ ማሰባሰቢያ እንቅስቃሴም ማድረጉ ታውቋል።

በመንግሥቱ መዘጋት ጉዳይ ላይ ዴሞክራቶቹ እንደራሴዎች ፕሬዚዳንቱንና ሪፐብሊካን ባልደረቦቻቸውን ሲወነጅሉ ሪፐብሊካኑ ደግሞ በዴሞክራቶቹ ሲያሳበቡ እየተሰሙ ናቸው።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG