በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዋሺንግተን ስድሣ የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ልታስወጣ ነው


ዩናይትድ ስቴትስ ስድሣ የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ለማባረር ወሰነች።

ዲፕሎማቶቹ በአንድ ሣምንት ጊዜ ውስጥ እንዲወጡ የተወሰነው “በስለላ አድራጎቶች ላይ ተሠማርተዋል” በሚል መሆኑን ከዋይት ሃውስ ቤተመንግሥት የወጣው ዘገባ ይጠቁማል።

አንድ ቀድሞ የሩሲያ ሰላይ የነበሩ ሰው ከሴት ልጃቸው ጋር ሳልስበሪ-እንግሊዝ ውስጥ ነርቭ አዋኪ በሆነ ጋዝ የተመረዙት “ከሞስኮ በወጣ ትዕዛዝ ነው” የሚል ዕምነት ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር የተጋሩ ሌሎችም የአውሮፓ ሃገሮች ተመሣሣይ እርምጃ መውሰዳቸው ታውቋል።

ፈረንሣይ፣ ጀርመንና ፖላንድ ከሃገሮቹ መካከል መሆናቸው ታውቋል።

ሞስኮን “የኬሚካል የጦር መሣሪያዎች ስምምነትን ጥሳለች፤ ዓለምአቀፍ ሕግን ረግጣለች” ሲል የከሰሰው የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ለዚህ “እጅግ አስቆጭ” ሲል ለገለፀው “አድራጎት” ምዕራብ ዩናይትድ ስቴትሷ ዋሺንግተን ግዛት ውስጥ የሚገኝ አንድ የሩሲያ ቆንስላም እንዲዘጋ መወሰኑን አስታውቋል።

ሴአትል ከተማ ውስጥ የሚገኘው የሩሲያ ቄንስላ እንዲዘጋ የተወሰነው ለቦይንግ ኩባንያ የአይሮፕላን ማምረቻና ኪትሳፕ ወደብ ላይ ላለው የዩናይትድ ስቴትስ ባሕር ወለድ መደብ ባሕር ሰርጓጅ ኒኩሌር መርከቦች መነሻ ባለው ቅርበት ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።

ዩናይትድ ስቴትስ ከሩሲያ ጋር የተሻለ ወዳጅነት እንዲኖራት ለመተባበር ዝግጁ መሆኗን ለጋዜጠኞች ያሳወቁት የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ሳራ ሃከቢ ሳንደርስ “ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ሩሲያ ጠባይዋን ካረመች ብቻ ነው” ብለዋል።

ዋሺንግተን የዛሬዎቹን እርምጃዎች የወሰደችው “ወታደራዊ ደረጃ ያለው ኬሚካል እንግሊዝ ምድር ላይ ጥቃት ለማድረስ በመጠቀሟ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ትብብር ድርጅት - ኔቶ አባል ሃገሮች የወሰዱትን እርምጃ በመደገፍ ነው” ሲሉ ቃል አቀባይዋ አመልክተዋል።

ሳልስበሪ ውስጥ ከተፈፀመው ጥቃት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው በመግለፅ የሩሲያ መንግሥት ውንጀላውን እያስተባበለ ይገኛል።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG