የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን እና ሩሲያ ልዩ ልዑክ፣ ለዩክሬን የጸጥታ ዋስትና እንደሚያስፈልግና ዩናይትድ ስቴትስም ጉዳዩን እንደምትረዳ ተናገሩ። ልዑኩ ይህን ያሉት በዛሬው ዕለት ከዩክሬን ባለሥልጣናት ጋራ ለመነጋገር ሀገሪቱን በጎበኙበት ወቅት ነው።
ጄኔራል ኪዝ ኬሎግ በዩክሬን የተገኙት የሀገሪቱን ባለሥልጣናት ስጋት "ለማዳመጥ" እና ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሲመለሱ ከፕሬዝደንት ትራምፕ ጋራ ለመማከር እንደሆነ ኪይቭ ላይ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ኬሎግ ዩናይትድ ስቴትስ በዩክሬን ያለው ጦርነት እንዲያበቃ እንደምትሻ ፣ይህም ለቀጠናው እና ለዓለም ጠቃሚ እንደሚኾን ተናግረዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በግጭቱ እና አውሮፓውያን ለዩክሬን በሚሰጡት ድጋፍ ላይ ለሁለተኛ ዙር ከአውሮፓ መሪዎች ጋራ መምከራቸውን ጨምሮ ፣ንግግሮቹ ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገውን ጦርነት በተመለከተ እየተካሄደ ያለው ተከታታይ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አካል ናቸው።
ኪሎግ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ከአውሮፓ መሪዎች ጋራ ተገናኝተዋል። ትናንት ማክሰኞ ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊ ማርኮ ሩቢዮ ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ከሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋራ ተነጋግረዋል።
ሩቢዮ ዩክሬን እና ሩሲያ ሰላምን ለማምጣት ስምምነት ማድረግ አለባቸው ብለዋል። ሩቢዮ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ዓላማው ይህንን ግጭት ፍትሃዊ፣ ዘላቂ እና ተቀባይነት ባለው መንገድ ማስቆም ነው" ብለዋል። በዚህ ውይይት ላይ የዩክሬን ወይም የአውሮፓ ባለሥልጣናት አልተገኙም።
የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ከስብሰባው መገለላቸውን ተቃውመዋል። ይህ አቋም የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን ትችት አስከትሏል።
“በውይይቱ አልተጋበዝንም' የሚል ዛሬ ሰምቻለሁ። በዚያው ለሦስት ዓመታት ቆይታችኃል" ሲሉ የዩክሬን መሪዎችን የተናገሩት ትራምፕ "ቀድሞውኑም መጀመር አልነበረባችሁም" ሲሉም አክለዋል።
በአውሮፓዊያኑ የካቲት 2022 ዓ.ም ነበር ሩሲያ ዩክሬን ላይ ባደረገችው ሙሉ ወረራ ጦርነቱ የተጀመረው።
ትረምፕ በፍሎሪዳ መኖሪያቸው ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፣ "ጦርነቱን ለማስቆም ጥሩ ዕድል አለኝ" ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል። ይሁንና ፕሬዝደንት ዜለንስኪ ሀገራቸው በዩናይትድ ስቴትስ እና ሩሲያ በሚወሰን የጦርነት እልባት አትስማማም።
መድረክ / ፎረም