በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአዮዋ ‘ኮከስ’፣ የአሜሪካ ምርጫና ዓለም አቀፍ አንድምታው


የአዮዋ ‘ኮከስ’፣ የአሜሪካ ምርጫና ዓለም አቀፍ አንድምታው
please wait

No media source currently available

0:00 0:10:01 0:00

የአዮዋ ‘ኮከስ’፣ የአሜሪካ ምርጫና ዓለም አቀፍ አንድምታው

ከሁለት ሣምንታት በፊት በተጀመረው የአውሮፓውያኑ 2024 ዓ/ም የቀን አቆጣጠር፣ በመላው ዓለም በሚገኙ በርካታ አገራት ምርጫ ይደረጋል። አራት ቢሊዮን የሚሆነው ወይም ከዓለም ሕዝብ ግማሹ፣ ወደ ምርጫ ጣቢያ በማቅናት ድምጽ ይሰጣል። ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ብዛት ያላቸው ድምጽ ሰጪዎች፣ በመላው ዓለም ወደ ተዘጋጁ የምርጫ ጣቢያዎች ይጎርፋሉ ተብሏል። ዲሞክራሲያዊ ነን የሚሉ አስተዳደሮችም የሚፈተኑበት ዓመት እንደሚሆን ተነግሯል።

ከባንግላዴሽ እስከ አሜሪካ፤ ከአውሮፓ እስከ ሜክሲኮ፤ ከእንግሊዝ እስከ ቀድሞ ቅኝ ግዛቷ እና በዓለም ትልቋ ዲሞክራሲ ተብላ በምትንቆለጳጰሰው ህንድ ምርጫ ይደረጋል። ጥቂቶቹም ባለፉት ሁለት ሣምታት ምርጫቸውን አከናውነዋል።

በዚህ ዓመት በመላው ዓለም የሚደረጉት ምርጫዎች፣ የዓለም አቀፍ ግንኙትንም ሆነ የየአገሪቱን ዕጣ ፈንታ ለመጪዎቹ በርካታ ዓመታት ይወስናሉ ተብሏል።

እንደ አሜሪካ ባሉ ጥቂት አገራት ውስጥ የሚደረጉ ምርጫዎች አንድ ምታ፣ በአገራቱ የውስጥ ፖለቲካ እና ፖሊሲ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በተቀረው ዓለምም ላይ ያላቸው ተጽእኖ ጉልህ እንደሆነ ይታመናል።

በአሜሪካ፤ የቀድሞ ፕሬዚደንት እና የሪፐብሊካን ፓርቲው እጩ ለመሆን ከፊት ረድፍ የሚገኙት ዶናልድ ትረምፕ፣ በርካታ የክስ ሂደት ላይ እያሉም፣ ከፍተኛ የፓርቲው እና የድምጽ ሰጪዎች ድጋፍ እንዳላቸው የሕዝብ አስተያየት መለኪያዎች ይጠቁማሉ። ትረምፕ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ የሆነላቸው አይመስልም። በኮሎራዶ ግዛት የሚገኘው ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ በእ.አ.አ ጥር 6፣ 2021 በአሜሪካ ምክር ቤት ላይ ከተደረገው አመጽ ጋር በተገናኘ፣ የሕገ መንግስቱን ማሻሻያ አንቀጽ 14 በመጥቀስ፣ በግዛቲቱ ምርጫ እንዳይሳተፉ ወስኗል።

የሕገ መንግስቱ ማሻሻያ አንቀጽ 14፣ በመንግሥት ላይ ያመጸ ወይም አመጹን የደገፈ ለፕሬዚደንትነት መወዳደር እንደማይችል ይደነግጋል።

ትረምፕ ጉዳዩን ወደ አገሪቱ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በመውሰድ አቤት ብለዋል። በአገሪቱ የመጨረሻው ፍርድ ሰጭ አካል የሆነው ጠቅላይ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን በመጪው የካቲት መጀመሪያ ላይ እንደሚመለከተው ይጠበቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ቀሪው የአሜሪካ የምርጫ ሂደት በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ቀጥሏል።

ባለፈው ሰኞ በአዮዋ ግዛት በተካሄደው እና አዮዋ ኮከስ ብለው በሚጠሩት - መራጮች የፕሬዚደንታዊ እጩን ለመምረጥ በየአካባቢያቸው ተሰብስበው የሚወያዩበት እና ድምጽ የሚሰጡበት ሂደት ተከናውኗል። የሪፐብሊካን ፓርቲው ባካሄደው በዚህ ምርጫም፣ የቀድሞ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ እስከ አሁን ያልታየ ከፍተኛ ድምጽ እንዳገኙ ታውቋል።

በአሜሪካ ምርጫ የአዮዋ ኮከስ ትልቅ ሥፍራን ይይዛል። የምርጫው ሂደት መጀመሩ የሚበሰርበት እና አብላጫ ድምጽ የሚያገኘው የያዘውን መሪነት የሚያጠናክርበት፣ ድምጽ ያላገኘው እጩ ደግሞ በውድድር ይቀጥል ወይም አቋርጦ ይወጣ እንደሁ የሚወስንበት ሂደትም ነው።

ስለ ኮከስ ምንነት የበለጠ ለመረዳት ቴክሳስ በሚገኘው ካሊን ኮሌጅ የኢኮኖክስ መምህር የሆኑትና በእ.አ.አ 2014 (ከአሥር ዓመታት በፊት መሆኑ ነው) በግዛቲቱ ለሴኔት ወይም ለሕግ መወሰኛው ምክር ቤት አባልነት የተወዳደሩትን ፕሮፌሰር ሞሃመድ ጣሂሮ አነጋግረናቸዋል።

በሌላ በኩል በአሜሪካ የሚደረጉ ምርጫዎች ውጤት በዓለም አቀፍ ግንኙነትም ሆነ በውጪ ጉዳይ ፖሊሲዎች ላይ ተጽእኖ እንደሚኖራቸው ይታመናል። ባለፈው ምርጫ፣ ከፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ ወደ ጆ ባይደን ሽግግር ሲደረግ፣ ለአፍሪካ ቀንድም ሆነ ለኢትዮጵያ መልካም ሊሆን እንደሚችል በበርካቶች ዘንድ ተስፋ ተደርጎ ነበር። ለመሆኑ ይህ ተስፋ ከምን የተነሳ የመጣ ነው? ተስፋውስ እውን ሆኗል ወይ ስንል ደግሞ፣ ትውልደ ኢትዮጵያ የሆኑት እና በዲሞክራሲው ፓርቲ የተመዘገቡ አባል፣ እንዲሁም ባለፉት በተደረጉ ሁለት ምርጫዎችም ፓርቲውን በመወከል የምርጫ ታዛቢ የነበሩትን አቶ ዳንኤል ውብሸት ጠይቀናል።

ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG