ቻይና፣ ሩሲያና ኢራን በአሜሪካ የሚደረገውን ምርጫ ውጤት ለመቀየር የተለያዩ የሳይበር ጥቃቶችን በመሞከር ላይ መሆናቸውን የሚያመለክቱ አዳዲስ መረጃዎች መገኘታቸው ታውቋል።
ማይክሮሶፍት እና ‘ሪኮርድድ ፊውቸር’ የተሰኘው የሳይበር ደህንነት ኩባንያ እንዳስታወቁት፣ ከሃገራቱ ጋራ ግኑኝነት ያላቸው ተዋንያን የምክር ቤት አባላትን የኮምፒውተር ሥርዓት ዒላማ አድርገዋል።
በተጨማሪም በማኅበራዊ ሚዲያ የመራጮችን ሃሳብ ለማስቀየር ሞክረዋል፣ በምርጫው እንዳይሳተፉም ቅስቀሳ አድርገዋል ተብሏል።
ማይክሮሶፍት እንዳስታወቀው፣ ከቻይና ጋራ ግንኙነት ያላቸው የሳይበር ተዋንያን ቢያንስ አራት የሪፐብሊካን ፓርቲ የምክር ቤት ዓባላትን ዒማላ አድርገዋል። አባላቱ የቻይናን መንግስት በመንቀፍ የሚታወቁ ናቸው።
ዋሽንግተን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ የማይክሮሶፍትን ውንጀላ ተቃውሟል።
የተወካዮች ም/ቤት አባላቱ ከቻይና ወገን የሳይበር ጥቃት ሙከራ መጨመሩ እንዳላስገረማቸው አስታውቀዋል።
ቻይና ብቻ ሳትሆን ከሩሲያ እና ኢራን ጋራ ግንኙነት ያላቸው የሳይበር ተዋንያን አንዳንድ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ዒላማ በማድረግ በአሜሪካ በሚደረገው ምርጫ ላይ ተጽእኖ ለማሳረፍ እየሞከሩ ነው ተብሏል።
ማይክሮሶፍት ጨምሮ እንደገለጸው “የሩሲያ የሳይበር ተዋንያን ከቴሌግራም ወደ X ማኅበራዊ ሚዲያ በመሸጋገር ተጨማሪ ድምፅ ሰጪዎችን ለማግኘትና መልዕክቶቻቸውን ለማዳረስ ችለዋል” ብሏል።
መድረክ / ፎረም