የዩናይትድ ስቴትስ የንግድ ሚኒስቴር የምጣኔኃብት ትንታኔ ቢሮ ትናንት ሐሙስ ባወጣው መረጃ በያዝነው 2022 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በ1 ነጥብ 6 ከመቶ ወርዶ የነበረው አጠቃላይ የሃገር ውስጥ ምርት ከሚያዝያ እስከ ሰኔ በነበሩት ሦስት ወራት ውስጥ በመጠኑ አንሠራርቶ በዜሮ ነጥብ ዘጠኝ ከመቶ ማዘቅዘቁን አሳይቷል።
የተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞችና አንዳንድ ኢኮኖሚስቶች የዩናይትድ ስቴትስ ምጣኔ ኃብት "የውድቀት ምልክቶችን አሟልቷል” ቢሉም ፕሬዚደንት ጆ ባይደንና ባለሥልጣኖቻቸው ግን የሚያምኑት ተቃራኒውን መሆኑን እየተናገሩ ነው።
የዩናይትድ ስቴትስ የንግድ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ የመንሸራተት ጠቋሚ በሆነ ሁኔታ የምጣኔ ኃብቱ ዕድገት ለሁለተኛ ተከታታይ ሩብ ዓመት መቀነሱን የሚያሳይ መረጃ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ባይደን በሰጡት መግለጫ የዓለም ንግድ መናኸሪያ በሆነው የኒው ዮርኩ "ዎል ስትሪትና ተንታኝ ጠቢባን መካከል ‘ውድቀት ውስጥ ነን አይደለንም’ በሚል ዛሬ ብዙ ሹክሹክታና ጉምጉምታ ይኖራል። ነገር ግን የሥራ ዕድል ገበያውንና የቅጥሩን ሁኔታ፥ ሸማቹ ገበያ ላይ የሚያወጣውን ገንዘብ፥ የመዋዕለ-ነዋይ ፍሰቱን መጠን ስናይ ግን በሁለተኛው ሩብ ዓመትም የምጣኔኃብት ዕድገት ምልክቶች መኖራቸውን እንመለከታለን" ብለዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሯ ጃኔት ዬልን ቀደም ብለው ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል "’የምጣኔኃብት “ድቀት” ውስጥ ነን አይደለንም’ በሚል በቃል አተረጓጎምና አጠቃቀም ላይ መነታረኩን እንተውና ምጣኔኃብታችን አደጋን የሚቋቋም ወይም ተለማጭ እንደሆነ ነው" ብለዋል።
የአሜሪካ ኢንተርፕራይዝ ኢንስቲትዩት የምጣኔ ኃብት ባለሙያው ዴዝሞንድ ላክማን ቀደም ሲል ለቪኦኤ በሰጡት ትንታኔ “የምጣኔ ኃብቱ ዕድገት ለሁለት ተከታታይ ሩብ ዓመት ማሽቆልቆል ካሳየ የውድቀት ምልክት እንደሆነ ብዙው ሰው ስለሚያምን በአብዛኛው አስተሳሰብ ‘ድቀት’ ላይ ነን” ብለው ነበር።
“በበረታው ግሽበት ምክንያት ሰዉ የኑሮ ትግል ላይ በመሆኑ፣ ገቢው እየተሸረሸረ በመምጣቱና በሸቀጦች ገበያ ላይም ብዙዎች በመክሰራቸው የሸማቹ መተማመን እጅግ ዝቅተኛ ሊባል በሚችል ደረጃ ወርዷል” ሲሉ ላክማን አክለዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የምጣኔኃብት ድቀት መከሰት አለመከሰቱን የሚበይነው ብሄራዊው የምጣኔ ኃብት ምርምር ቢሮ ቢሆንም ውሣኔው የሚቆረጠው ያለፉ ሁኔታዎች ተገምግመውና ግምት ውስጥ ገብተው መሆኑ ይነገራል።
የቢሮው የኢኮኖሚ ውድቀት ትርጓሜ የሚመሠረተው የሥራ ዕድሎች መኖርና አለመኖርን፣ የምጣኔኃብቱን ተዋፅዖ፣ የችርቻሮ ንግድን እንቅስቃሴ፣ የቤተሰብ የነፍስ ወከፍ ገቢን ግምት ውስጥ አስገብቶ ባለፉ በርካታ ወራት ውስጥ በምጣኔኃብቱ ላይ ግዙፍ የሚባል መንሸራተት ተመዝግቦ ከሆነ በሚወጡ መረጃዎች ላይ መሆኑን ቢሮው ይጠቁማል።
አንዳንዶች የዩናይትድ ስቴትስ ምጣኔኃብት እርስ በርስ የሚቃረኑ የሚመስሉ ገፅታዎች ያሉት እንደመሆኑ አንዱን ገፅታ ብቻ ተመርኩዞ በቀላሉ መደምደም አይቻልም ሲሉ ይከራከራሉ።
የገንዘብ ግሽበቱ በአርባ ዓመታት ውስጥ ባልታየ መጠን እያሻቀበ ቢሆንም በየወሩ በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች እየተከፈቱ መሆናቸውንና የሥራ አጥነት መጠኑም በሃምሳ ዓመታት ውስጥ ባልታየ ሁኔታ ወደ 3 ነጥብ 6 ከመቶ ማሽቆልቆሉን እንደማሳያ በማውጣት ይሟገታሉ።