በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአሜሪካ የወደብ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማቸውን አቋረጡ


ኮንቴይነሮች በኒው ጀርሲ ፖርት፣ ኒው ዮርክ
ኮንቴይነሮች በኒው ጀርሲ ፖርት፣ ኒው ዮርክ

በአሜሪካ ለሦስት ቀናት የሥራ ማቆም አድማ ላይ የነበሩት የወደብ ሠራተኞች ለአዲስ የሥራ ኮንትራት የድርድር ጊዜ ለመስጠት በሚል እ.አ.አ እስከ ጥር 15፣ 2025 ድረስ አድማቸውን ለማቋረጥ ተስማምተዋል። ወዲያውኑ ወደ ሥራቸው እንደሚመለሱም የሠራተኛ ማኅበሩ አስታውቋል።

ከሜይን እስከ ቴክሳስ ግዛቶች በሚገኙ ወደቦች የሚያገለግሉና 45 ሺሕ ዓባላት ያሉት የወደብ ሠራተኞች ማኅበር አድማ፣ 36 ወደቦች ላይ መስተጓጎል ሊፈጥር ይችል እንደነበር ታውቋል።

የሥራ ማቆም አድማው የተቋረጠው የሠራተኛ ማኅበሩና የአሜሪካ የወደቦች ኅብረት በደመወዝ ጭማሪ ላይ ጊዜያዊ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ መሆኑን ሁለቱ ወገኖች በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ሥምምነቱን በተመለከተ ማብራርያ እንደተሰጣቸው የገለጹና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ግለሰብ፣ በቀጣይ 6 ዓመታት ውስጥ የደመወዝ መጠን በ62 በመቶ እንዲጨምር ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል።

አድማው ከጥቂት ሳምንታት በላይ የሚዘልቅ ቢሆን ኖሮ የዋጋ ግሽበትን እና የሸቀጥ እጥረትን ሊያባብስ ይችል ነበር ተብሏል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG