በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ በቱርክ የተያዙት አሜሪካዊ ዲፕሎማት አይደሉም አለች


ፎቶ ፋይል፦ የዩኤስ ፓስፖርት
ፎቶ ፋይል፦ የዩኤስ ፓስፖርት

ዩናይትድ ስቴትስ የቱርክ ባለሥልጣናት የሀሰት ፓስፖርት ሽያጭ በመጠርጠር ይዘናዋል ያሉት ሰው የዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማት አለመሆኑን አስታወቀች፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ትናንት ረቡዕ በሰጡት መግለጫ "በቱርክ ስለታሰረው የዩናይትድ ስቴትስ ዜጋ እናውቃለን፡፡ ግለሰቡ የዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማት አይደሉም፡፡ እኛ ተገቢውን የቆንስል አገልግሎት እየሰጠን ነው" ብለዋል፡፡

በቱርክ የኢስታንቡል ፖሊስ ለሶሪያ ዜጎች የሀሰት ፓስፖርቶችን በመሸጥ የተጠረጠሩት ግለሰብ በፖስታ ከታሸገ 10 ሺ ዶላር ጋር የተያዙት እኤአ ህዳር 11 መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ግለሰቡ ልብስ ሲለዋወጡ የሚያሳይ በደህንነት ቪዲዮ ካሜሪ የተቀረጸ ማስረጃ መኖሩንም ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የቱርክ ባለሥልጣናት ዲጄኬ በሚል ምህጻረ ቃል ብቻ የጠሩት ግለሰብ ቤይሩት በሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ሠራተኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የሶሪያው ዜጋም በዲጄኬን ፓስፖራት ተዘጋጅቶ የተሰጣቸውን ስም በመጠቀም ወደ ጀርመን ለመብረር ሲዘጋጁ የተያዙ መሆኑን የቱርክ መንግሥት ዜና ወኪል አናዶሉ ዘግቧል፡፡ የሶሪያው ዜጋ በሰነድ ማጭበርበር የተከሰሱ ሲሆን በዋስ መለቀቃቸው ተመልክቷል፡፡

ቱርክ እኤአ በ2016 ተደረጎ በከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት ተባባሪ ሆነዋል ያለቻቸውን የዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማት ሠራተኞን ያሰረችበትን አጋጣሚ ጨምሮ በቱርክና በዩናይትድስቴትስ መካከል ያለው ግንኙነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየሻከረ መምጣቱ ይነገራል፡፡

XS
SM
MD
LG