በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚንስትር በድንገት ኢራቅን ጎበኙ


የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚንስትር ሎይድ ኦስተን፣ የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ሺያ አልሱዳኒ
የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚንስትር ሎይድ ኦስተን፣ የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ሺያ አልሱዳኒ

የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚንስትር ሎይድ ኦስተን ዛሬ ማክሰኞ በኢራቅ አስቀድሞ ያልተገለጸ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ ሚኒስትር ኦስተን ባደረጉት ንግግር ኢራቅ ውስጥ የተሰማሩ የዩናይትድ ስቴትስ ኃይሎች ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራውን ቡድን ድል ለመምታት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጸው ተልዕኮውን ለማከናወን ደህንነታቸውን መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

"ጸረ ዳኢሽ ትብብራችን የሁለቱ ሀገሮቻችን ግንኙነት ቁልፍ ምሰሶ ነው" ያሉት ሚንስትሩ ዩናይትድ ስቴትስ በኢራቅና በአጠቃላይ በክልሉ ጸጥታ እንዲሰፍን የሚደረገውን ትግል ማገዟን እንደምትቀጥል ገልጸዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚንስትር በቆይታቸው ከኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ሺያ አልሱዳኒ ጋር ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን የኢራቅን መሪዎች የህብረቱን ኃይሎች ደህንነት መንግሥታዊም መንግሥታዊ ካልሆኑ አካላት ጥቃት ለመጠበቅ ስላላቸው ቁርጠኝነት አመስግነዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ኃይሎች እና ባግዳድ ውስጥ የሚገኘው ኤምባሲዋ በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎች የሮኬት ጥቃት ኢላማ ሲያደርጓቸው ቆይተዋል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ኢራቅ ውስጥ 2500 ወታደሮች ያሏት ሲሆን ተልዕኳቸውም የኢራቅን ኃይሎች ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር በሚያካሂዱት ውጊያ ማማከር እና መርዳት መሆኑ ተመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG