በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አሜሪካ ብድሯን መክፈል ካልቻለች በመላው ዓለም የገንዘብ ቀውስ እንደሚከሠት ተጠቆመ


አሜሪካ ብድሯን መክፈል ካልቻለች በመላው ዓለም የገንዘብ ቀውስ እንደሚከሠት ተጠቆመ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:08 0:00

አሜሪካ ብድሯን መክፈል ካልቻለች በመላው ዓለም የገንዘብ ቀውስ እንደሚከሠት ተጠቆመ

የአሜሪካ መንግሥት የዕዳ ጣሪያውን መጠን ከፍ ለማድረግና ብድሩን መክፈል እንዲችል፣ በፕሬዚዳንት ጆ ባይደንና በኮንግረስ አመራሮች መካከል፣ ትላንት ማክሰኞ የተካሔደው ውይይት ያለውጤት ተበትኗል፡፡

በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ስምምነት ላይ የማይደረስ ከኾነ፣ የአሜሪካ መንግሥት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ብሔራዊ ዕዳውን ሳይከፍል ይቀራል፡፡ ይህም በመላው ዓለም የገንዘብ ቀውስ እንዲከተል ያደርጋል።

ይኸው ስጋት በአንዣበበትና መፍትሔ ለመስጠት የቀረው ጊዜ በሳምንታት በሚቆጠርበት በዚኽ ወቅት፣ ፕሬዚዳንት ባይደን፣ የዓለም ገበያን ለማረጋጋት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ “ብድራችንን መክፈል አለመቻል አማራጭ እንዳልኾነ፣ በስብሰባው ወቅት ግልጽ አድርጌያለኹ፤ ያን ደጋግሜ ተናግሬአለኹ፤” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ አሜሪካ ብድሯን ላለመክፈል የምትጥር እንዳልኾነች ተናግረዋል፡፡

ላለፉት በርካታ ወራት መፍትሔ ሳይገኝለት ለቀረውና አገሪቱ ዕዳዋን መክፈል ትችል ዘንድ መበደር የምትችለውን የገንዘብ መጠን ከፍ ለማድረግ፣ ፕሬዚዳንት ባይደን ከምክር ቤት መሪዎች ጋራ፣ ትላንት ከቀትር በኋላ ስብሰባ ቢቀመጡም፣

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ፣ ሪፐብሊካኑ ከቭን ማካርቲ፣ ሌሎች ወጪዎች ካልቀነሱ በሚል፣ የብድር ጣሪያውን ከፍ ለማድረግ ሳይስማሙ ቀርተዋል፡፡

ምክር ቤቱ፥ የብድር ጣሪያውን፣ ሓላፊነት በተሞላው መንገድ ከፍ ማድረጉን የገለጹት አፈ ጉባኤው፣ “ወጪያችንን ለመቀነስና የኢኮኖሚ እድገትን ለማምጣት” በማለት ካስረዱ በኋላ፣ ለፕሬዚዳንቱ ቀላል ያሉትን ጥያቄ አቅርበዋል፤ “ወጪያችንን የምንቀንስበት ሌላ መንገድ የለም ብለው ያምናሉ?” የሚል።

አሜሪካ የብድር ጣሪያዋን ከፍ ማድረግ ሳትችል ከቀረች፣ በአገሪቱ የኢኮኖሚ ድቀትን ከማስከተሉም በተጨማሪ፣ በመላው ዓለም ባለው የመዋዕለ ነዋይ ገበያ ላይ ቀውስን እንደሚያስከትል፣ የዋይት ሓውስ ቃል አቀባይ ካሪን ዣን ፒዬር ያስጠነቅቃሉ፡፡ “ብድርን አለመክፈል፥ በዓለም የአሜሪካ ዶላርን ዋጋ፣ የአሜሪካን ተቋማትንና አመራር በተመለከተ መተማመን እንዳይኖር ያደርጋል፤” ሲሉ የሚመክሩት ቃል አቃባዩ፣ ዋጋቸው በዶላር በተተመነው በገንዘብ ዝውውር እና በሸቀጥ ገበያ ላይ ቀውስን ሊፈጥር እንደሚችል አመልክተዋል፡፡

በዓለም ትልቁ የኾነው የአሜሪካ ኢኮኖሚ፣ ዶላሩም በዓለም ተመራጭ መገበያያ ነው፡፡ አሜሪካ ዕዳዋን ሳትከፍል ከቀረች፣ ግምጃ ቤቱ ቦንዱን በቅናሽ እንዲሸጥ ይገደዳል፤ የዶላርን ዐቅም ያዳክማል፤ የወለድንም መጠን ይጨምራል፤ ሲሉ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ዴዝመንድ ላችማን፣ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የቀድሞ ምክትል ዲሬክተር ሲኾኑ፣ አሁን በአሜሪካ የንግድ ተቋም ተመራማሪ ናቸው፡፡“በአሜሪካ የወለድ መጠን ከፍ ካለ፣ የሌሎችም ነገሮች የወለድ መጠን ከፍ ይላል፤ የንብረት ዋጋም አስተማማኝ እንዳይኾን ያደርጋል፤” ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

የአሜሪካ ግምጃ ቤት ቦንድ፣ በተለምዶ ለመዋዕለ ነዋይ ደኅንነት አስተማማኝ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቀድሞ የኢኮኖሚ ባለሞያ፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የውጭ ግንኙነት ም/ቤት በተሰኘው ተቋም ተመራማሪ ሃይዲ ክሬቦ-ሬዲከር እንደሚሉት፣ ቀውሱ እንዳለ ኾኖ፣ ሀገራት እና ባለሀብቶች፣ የአሜሪካ ዕዳ አለመክፈል ከሚገባው በላይ ሊያሳስባቸው አይገባም፡፡ አያይዘውም፣ “ይህ ለመክፈል ያለንን ፈቃደኝነት እንጂ የመክፈል ችሎታን የተመለከተ ጥያቄ አይደለም፡፡ ብድርን አለመክፈል፣ ከእነዚኽ ከሁለቱ ነገሮች አኳያ ነው መታየት አለበት፤” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ባይደንና የም/ቤቱ መሪዎች ዓርብ ለመገናኘት ሌላ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡

የቪኦኤ የዋይት ሓውስ ዘጋቢ ፓትሲ ዊዳኩስዋራ ያጠናቀረችውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

XS
SM
MD
LG