ዩናይትድ ስቴትስ ሩሲያን ዒላማ ያደረጉ በመቶዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ማዕቀቦች መጣሏን ረቡዕ እለት አስታውቃለች። ማዕቀቦቹ ሩሲያ የሚጣሉባትን ማዕቀቦች ለማለፍ የምታደርገውን ጥረት ለመመከት አሜሪካ ቁርጠኛ መሆኗን እንደሚያሳይ ተመልክቷል።
የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ባወጡት መግለጫ፣ ወደ 400 የሚጠጉ ተቋማት እና የተለያየ አገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ መጣላቸውን ገልጸዋል። ማዕቀቡ ከተጣለባቸው መካከል በርካታ የቻይና፣ ሆንግ ኮንግ እና ህንድ ኩባንያዎች እንደሚገኙበትም አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣን ለሮይተርስ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በሩሲያ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ በቱርክ፣ በታይላንድ፣ በማሌዥያ፣ በስዊዘርላንድ እና በሌሎች ሀገራት የሚገኙ ተቋማት ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።
ጥቃቅን ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ጨምሮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና የአውሮፓ ህብረት የላቁ ያሏቸውን እና ሩሲያ ለዩክሬን ወረራ ልትጠቀምባቸው የሚችላቸውን ምርቶች፣ ሀገራት ለሩሲያ እንዳያቀርቡ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በተደጋጋሚ ስታስጠነቅቅ ቆይታለች።
ስማቸው እንዳይገለፅ የጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ባለስልጣን፣ ማዕቀቡ "ለመንግስታትም ሆነ በነዚህ ሀገራት ለሚገኙ የግል ኢኮኖሚ ዘርፎች፣ ሩሲያ የሚጣልባትን ማዕቀብ ለመሸሽ የምታደርጋቸውን ጥረቶች ለመመከት ቁርጠኛ መሆናችንን የሚያሳይ መልዕክት ሊያስተላልፍ ይገባል" ብለዋል።
ማዕቀቡ ዒላማ ካደረጋቸው ተቋማት መካከል መቀመጫውን ህንድ ያደረገው 'ፉትሬቮ' አንዱ ሲሆን፣ ሩሲያ ለሚገኘው የሰው ሰራሽ አውሮፕላን (ድሮን) አምራች ኩባንያ እጅግ ተፈላጊ የሆኑ ቁሶችን በማቀርብ ክስ ቀርቦበታል።
መድረክ / ፎረም