ዋሺንግተን ዲሲ —
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የተሰናባቹን ፕሬዚዳንት የኮቪድ-19 ክትባት መርሃ ግብር ነቀፉ።
ጆ ባይደን ትናንት በብሄራዊ የጤና ተቋም /ኤንአይኤች/ ባሰሙት ንግግር አሜሪካውያንን ችግሩን እስከማስተካክል ድረስ ታገሱኝ ሲሉ ተማጽነዋል።
"ፍርጥ አድርጌ ነው የምናገረው፥ ከኔ በፊት የነበሩት ፕሬዚዳንት ለብዙ ሚሊዮን ህዝብ ክትባቱን በማቅረብ ረገድ ያለውን የከበደ ፈተና ለመጋፈጥ ጥሩ ሥራ አልሰሩም" በማለት የነቀፉት ጆ ባይደን ያን ማስተካከሉ ጊዜ ይጠይቃል፤ ታገሱኝ " ሲሉ ተማጽነዋል።
አክለውም ባይደን ዩናይትድ ስቴትስ ከሦስት መቶ ሃያ ስምንት ሚሊዮኑ ህዝብ መካከል ሦስት መቶ ሚሊዮኑን እስከ መጪው ሃምሌ በሚኖረው ጊዜ ውስጥ ለማዳረስ የሚበቃ ክትባት አግኝታለች ብለዋል።
ጆ ባይደን በመጀመሪያው የአስተዳደራቸው የአንድ መቶ ቀን ጊዜ አንድ ሚሊዮን ሰው ይከተባል የሚል ግብ ይዘው ነበር፤ አሁን ባለው አካሄድ እንደሚታየው ከዚያ በላይ ህዝብ ይከተባል።
የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል /ሲዲሲ/ እንዳስታወቀው እስካሁን ከአርባ ስድስት ሚሊዮን የሚበልጥ ክትባት ተሰጥቷል።