የእስልምና አክራሪዎች በመላው ዓለም እየደቀኑ ያለው ስጋት እየጨመረ ሲሆን፣ ስጋቱን ለመከላከል የሚያስፈልገው ኅይል ግን እየተመናመነ መሆኑን አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ የፀረ ሽብር ባለሥልጣን አስታወቁ።
የአሜሪካ የፀረ ሽብር ቢሮ ኃላፊ እና የፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ልዩ ረዳት የሆኑት ሰባስቲያን ጎርካ፣ ባለፉት ሦስት ሳምንታት ወቅታዊውን የሽብር ስጋት አስመልክቶ ግምገማ ማድረጋቸውንና ይህም አሁናዊውን የሽብር ስጋት ለመረዳት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
እንደ ከፍተኛ የጸረ ሽብር ባለሥልጣኑ ገለጻ፣ በቁጥር አንድ የሚጠቀሰው የእስልምና አክራሪ ቡድኖች የሚገኙባቸው ሥፍራዎች እየጨመረ መምጣት ሲሆን፤ ትስስራቸው በሳህል፣ በመካከለኛውና መሥራቅ አፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እንዲሁም በመካከለኛው እስያ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
እንደ ምሳሌም በምዕራብ አፍሪካ ያለውን ሁኔታ አንስተዋል። “ከዚህ በፊት የእስልምና አክራሪዎች ስጋት እምብዛም የማይታይባቸው እንደ ቤኒን እና ቶጎ ያሉ የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት፣ አሁን የሱኒ እስልምና አክራሪዎች በድንበሮቻቸው ውስጥም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች ይገኛሉ። ይህም ብሔራዊ ሉአላዊነታቸውን ስጋት ላይ ጥሏል” ብለዋል ጎርካ።
ቤኒን እና ቶጎ በአል ቃይዳ ነውጠኖች ጥቃት እንደደረሰባቸው ከዚህ በፊት አስታውቀዋል።
በአሜሪካ የውጪ ፖሊሲ ም/ቤት የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ/ም በተዘጋጀ ኮንፈረንስ ላይ የተናገሩት ሰባስቲያን ጎርካ፣ በሁለተኛነት ያስቀመጡት ደግሞ የእስልምና አክራሪ ቡድኖቹ የግድያ ተልዕኳቸውን ለመፈጸም ቴክኖሎጂን የመጠቀም ብቃታቸው እየጨመረ መምጣቱን ነው።
በሦስተኛነት ደግሞ፣ ነውጠኞቹ አዲስ የሚወጡ የማኅበራዊ ሚዲያ ውጤቶችንና መልዕክትን በሚስጥር የሚልኩ መተገበሪያዎችን ወዲያውኑ የመጠቀም ብቃታቸው እንደሆነ ባለሥልጣኑ አመልክተዋል።
የወቅቱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ከገቡት ቃል አንዱ የድንበር ቁጥጥርን ማጥበቅና ሕገ ወጥ ፍልሰተኞችን ወደ ሃገራቸው መመለስ ሲሆን፣ ለዚህም ወደ ሥልጣን እንደተመለሱ ድንበርን የተመለከተ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀው ፕሬዝደንታዊ ትዕዛዝ ፈርመዋል።
ሰባስቲያን ጎርካ ከዚሁ ጋራ የሚያያዘውን ጉዳይ በአራተኛነት አንስተዋል። “በመላው ዓለም የሚገኙ የእስልምና አክራሪ ቡድኖች፣ በመላው ዓለም የሚታዩትን የደህንነት ክፍተቶች ይጠቀማሉ። በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት በደቡብ የሃገሪቱ ክፍል ድንበር አልነበረንም” ሲሉ ተናግረዋል ጎርካ።
የቀድሞው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ሁለቱ ፓርቲዎች በጋራ ሊያወጡት የነበረው የስደተኞች ሕግ፣ ከሪፐብሊካኑ ወገን ድጋፍ ባለማግኘቱ ውድቅ ሲሆን፣ የእርሳቸው የስደተኞች ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን እንዳልቻለ፣ ላለመሳካቱም የፕሬዝደንት ትረምፕ እጅ እንዳለበት በመግለጽ ፖሊሲያቸውን መከላከላቸው ይታወሳል
ጎርካ በገለጻቸው፣ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙና እንደ ሐማስና ሄዝቦላ የመሰሉ ቡድኖች በከፍተኛ ደረጃ እንዲዳከሙ መደረጉንና ቀጠናውም በዛው መጠን መቀየሩን አውስተዋል።
በጥቅምት 2016 የተፈጸመውን የሐማስ ጥቃት በማስታወስ የተናገሩት ጎርካ፣ ከ1945 ወዲህ በርካታ አይሆዶች የተገደሉበት እንደሆነ ጠቅሰው፣ በእስራኤል ያሉና “አጋሮች” ብለው የጠቀሷቸው ወገኖች “የቀጠናውን ካርታ እንደ አዲስ ሰርተውታል” ብለዋል።
ሐማስ በእስራኤል ላይ በሰነዘረው ጥቃት 1ሺሕ 200 ሰዎች ሲገደሉ፣ 250 የሚሆኑትን ደግሞ በእገታ ይዞ ነበር። እስራኤል በምላሹ በፈጸመችው ጥቃት ከ48 ሺሕ 200 በላይ ፍልስጤማውያን እንደተገደሉ የጤና ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። ከእነዚህም ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶችና ሕፃናት መሆናቸውን የፍልስጤም ባለሥልጣናት ሲገልጹ፣ እስራኤል በበኩሏ ከተገደሉት ውስጥ 17 ሺሕ የሚሆኑት ነውጠኞች እንደሆኑ ትገልጻለች፡፡
የሄዝቦላ እና ሐማስ ታጣቂዎች በከፍተኛ ደረጃ እንዲዳከሙ መደረጉ፣ በሶሪያ የአሳድ አገዛዝ እንዲንኮታኮት ማድረጉንና በዚህም በመንግሥታዊ የሽብር ደጋፊነት የሚታውቀው አገዛዝ እንዲያከትም መደረጉን፣ እንዲሁም ኢራን በአሜሪካ እና በአጋሮቿ ላይ ልታደርስ የምትችለው ጉዳትም አብሮ እንዲቀንስ ጎርካ ውስተዋል።
ጎርካ በተጨማሪም በፕሬዝደንት ትረምፕ ትዕዛዝ በሶማሊያ በሚገኙ የእስላማዊ መንግስት ቡድኖች ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሙን፣ ዋና የጥቃት አቀናባሪውን አህመድ ማሌኒኒኔን ጨምሮ 14 የቡድኑ ዓባላት መገደላቸውን አስታውሰዋል። አህመድ የኦማን ዜጋ መሆኑን የሶማሊያ ባለሥልጣናት ቢገልጹም፣ አሜሪካ በግለሰቡ ዜግነት ላይ ያለችው የለም። ጥቃቱም በቀይ ባሕር ከሚገኘው የአሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ላይ በተነሱ ተዋጊ ጄቶች መፈጸሙ ታውቋል።
ፕሬዝደንት ትረምፕ ጥቃቱ እንዲፈጸም ማዘዛቸውን ሲያረጋግጡ፣ ጎርካ በወቅቱ ፕሬዝደንቱ የተጠቅሙትን አገላለጽ ደግመዋል።
“አሜሪካውያንን የምትገድሉ ከሆነ፣ ወዳጆቻችንን የምትገሉ ከሆነ፣ አታመልጡንም፣ እናገኛችኋለን፣ እንገድላችኋለን” ሲሉ ጎርካ የትረምፕን ቃል ደግመዋል።
በፑንትላንድ የሚገኙ የሶማሊያ ኅይሎች በነውጠኞች ላይ የተሳካ ጥቃት ማድረሳቸውን በዚህ ሳምንት አስታውቀዋል። በአሥር የሚቆጠሩ ሲገደሉ፣ ነውጠኞቹ ውስብስብ የሆነ ጥቃት ለመፈጸም ያደረጉትን ዝግጅት ማክሸፋቸውንም አስታውቀዋል።
አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ካለፈው አስተዳደር አንጻር 30 በመቶ ባነሰ ኅይል በመላው ዓለም የሚገኙ የእስልምና አክራሪዎችን እየተፋለመ እንደሚገኝም የአሜሪካ የፀረ ሽብር ቢሮ ሃላፊው ሰባስቲያን ጎርካ አስታውቀዋል።
መድረክ / ፎረም